የአማራ ህዝብ ትግል አይደራደርም!!! (ፍፁም አየነው)

የአማራ ህዝብ ትግል አይደራደርም!!! (ፍፁም አየነው)

የነገን ተስፋ መገንባት ሚቻለው ዛሬ በምንሰራው ትልቅ ስራ ነው፡፡ተስፋ በተግባር ስራ መመስረት አለበት፡፡ያላከበርካት ዛሬ ፤ነገ አታከብርህም፡፡ የትግል ፍሬ በሂደት የሚመጣ እንጂ በአንድ ጀንበር የሚሞላም ሆነ የሚፈፀም አይደለም፡፡ ….የጀመርከውን የትግል ፍሬ ባልመረጥከው ሁኔታ ጠላትህ ይሰጠኛል ብለህ ምታስብም ሆነ ምጠብቅ ከሆነም ያኔ አንተ ሞተሃል….፡፡ጠላትህ ያለ ጦርነት የማረከህ ታጋይ ማለት አንተ ነህ፡፡የአራጆችህ እና የጮሌ ጠላቶችህ መሪነትና ዳኝነት ውስጥ ጭላንጭል ነፃነት አታገኝም፡፡አገኘው ብትል እንኳ ወይ ብልጭልጭ ወይ ወጥመድ ነው፡፡የሰው ልጅ ለነፃነት መታገል ተፈጥሯዊው ባህሪው ቢሆንም ጠላትህን አሸነፍኩ ማለት የምትችለው ነፃነትህን በእጅ ይዘህ ነው፡፡ያለ ትግል የምታመጣው ነፃነት ተንበርካኪነት ፣ተገዢነት ነው ሊሆን የሚችል…. ስለ ምንም ጉዳይ ብለህ ትግል ችላ ማለትም ነፃነት አሳልፎ ለመስጠት መዘጋጀት ነው፡፡ራስ ላይ ጦርነት ማወጅም ነው፡፡ በእጅ የሌለ ነፃነት ድል የለበትም ደግሞም ሆሮበትም አያውቅም፡፡
ማንም ሰው በሰራው ልክና መጠን ነው ውጤት ሚያገኘው ማለትም በትክክለኛው አሰራር እና ሂደት እስከሰራ ድረስ፡፡በትግል መስመርም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ስለዚህ ማንኛውም ታጋይ ትግል ከእራሱ ነው መጀመር ያለበት በታገለበት መጠን ደግሞ ያሸንፋል፡፡ራሱን ማወዳደር ያለበትም ከእርሱ በተቃራኒ ከተሰለፈ ጠላቶቹ እና ተቀናቃኞቹ ጋር ነው እንጂ ከሚበልጡት ወዳጆቹ ጋር መሆን የለበትም፡፡ በጣርነው ልክ እናሸንፋለን፡፡በአባከነው ጊዜና ስራ መጠንም ዋጋ እንከፍልበትለን፡፡
የሰው ልጅ ከትግል ውጭ ሆኖ መኖር አይችልም፡፡ በአለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥም ቢሆን፡፡ በአለማዊ ህይወቱ በኑሮ ሂደቱ ፣በምጣኔ ሃብት አቅሙ ፣ነፃነትን ፍለጋ ፣በቤተሰባዊ አስተዳደርም ሆነ ራስን ከመምራት ጀምሮ ካሉ ሀላፊነቶች ጨምሮ ይታገላል፡፡በመንፈሳዊ ህይወቱም ቢሆን ከህገ መፅሃፍ ቅዱስ ፣ህገ ቁርዓን ፣ህገ አቅዳስ….ወዘተ ከሚያሰናክሉት አለማዊ ፍላጎቶችም ሆነ ሰይጣን ጋር በትግል ፍልሚያ ውስጥ ነው ሚያልፈው፡፡
የአማራው ትግል በዚህ ወቅት ጀግኖቹንና ታጋዮቹን ከምንም እና ከመቼም ጊዜ በላይ ይፈልጋቸዋል፡፡
የአማራ ህዝብ ንጉሡን መሾምም ሆነ ጠላቱን አውርዶ ማርገፍ ያውቅበታል፡፡ወደ ድል በተጠጋህ መጠንም ብዙ ነገሮች በጠላት ወገን ያለ አሰላለፍም ይለዋወጣል፡፡አንተም ከጠላትህ ባህሪ አንፃር ትግልህን መምራትህንና ማጠንከርህን አትርሳ፡፡
የምታገኘቸውን ትናንሽ ድሎች ለማጣጣም ምትፈልግ ከሆነ ጠላትን ለአፍታም አትናቅ አትዘናጋለት በትኩረት አይን፣ሙሉ አዕምሮህን ተጠቅመህ ታገለው፡፡ባገኘኸው ትናንሽ ድሎችም ከመጠን ባለፈ አትርካ፡፡እያንዳንዱ ድካምህ ዋጋ አለው፡፡ስትታገል ብዙ ነገሮች ካሰብካቸው ቦታ ላታገኛቸው ብንችል እንኳን ሊገርሙህ አይገባም፡፡
የሚወድቀውን ጓድህን(ወዳጅህን) ለማንሳት በሙሉ ጥንካሬህ ሳትዘናጋ ተራመድ፡፡ እያንዳንዱ የአማራ ልጅ ምትክ የሌለው የማይወዳደር ከፍተኛውንና መራራ ፅዋ የሚቀበልበትን ትግል የስነ ልቦና አቅም መፍጠር ብሎም ክንዱን ማበርታትም ይኖርበታል፡፡ ወታደራዊ የአቅም ጉልበታ እና ፍጥነት በዚህ ወቅት የሚታየውን የሚንከባለል የፓለቲካ ምስቅልቅል ይፈታዋል፡፡አማራም በዚህ ወቅት ከተቃጣበት ሁሉን አቀፍ የጥቃት እና የጥፋት ዘመቻ እሱም በተመሳሳይ በሁለገብ አደረጃጀት እና ስልቶች ጠላቶቹን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት በድል ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ይኖበታል፡፡የአማራ ህዝብ ትግል አይደራደርም፡፡ ጠላቶቹም ስራቸውን እየጨረሱ ወደ አንድ ካንፕ እንተሰበሰቡ ነው፡፡ምንም ያህል ቢሰበሰቡ ድንጋይ ውሃ ላይ አይዋኝምና ወደ ጥልቁ ይወርዳሉ፡፡
ላናሸንፍ የጀመርነው ትግል የለም!!!