በአባይ ላይ ያለኝን መብት ለመከላከል ኃይሉም ቁርጠኝነቱም አለኝ – ግብጽ


የመረጃ ቲቪን 24/7 የሳተላይት ስርጭት በመደገፍ የኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ እና ትክክለኛ መረጃ በማግኘት እራሱን ከተጋረጠበት አደጋ መከላከል እንዲችል እናግዝ። በአሁኑ ወቅት ከመረጃ ቲቪ በስተቀር ሌሎች ሁሉም በኢትዮጵያ ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመንግስት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ናቸው። ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ የከፈትነው የመረጃ ቲቪ የሳተላይት ስርጭት የአንድ ዓመት ወጪን ለመሸፈን ነው። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ድጋፍዎትን ይለግሱ » https://gofund.me/54405070

BBC Amharic : በትናንትናው ዕለት መስከረም 28፣ 2012 የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹኩሪ ፓርላማ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ላይ የውሃ ሙሌቱን መቀጠሏ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በኦፕሬሽኑ ቀጥላለች፤ የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት መቀጠሏ ተቀባይነት የለውም። ይህ ተግባር የተደረሰውን ስምምነት የሚጥስ እና በቀጠናው ላይ አለመረጋጋትን በመፍጠር አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል” በማለት አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም “ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ሁሉንም አካላት የሚያስማማ መፍትሄ በማፍለቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን” ማለታቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ መስከረም 23 እና 24 በህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ የተደረገውን የሦስትዮሽ ምክክር ተከትሎ ግብፅ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቅርባ ነበር።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፤ በሦስቱ አገራት መካከል የተደረሱ አበረታች ስምምነቶችን የሚያፈርስ ከመሆኑ በተጨማሪ ሦስቱ አገራት በመጋቢት 2017 የፈረሟቸውን የመግለጫ ስምምነቶችም ይጥሳል በማለት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ገልፃለች።

ግብፅ ማን አደራዳሪ ይሁን በሚለው ላይ ምንም ባትልም የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ፤ አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላት ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

ግብፅ ዓለም ባንክ ሶስተኛ ወገን ሆኖ ልዩነቶችን በመፍታት እንዲያደራድር ግብፅ ምክረ ሃሳብ እንደምታቀርብ የግብፁ አሀራም ኦንላይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በትናንትናው ዕለት ሳሚህ ሽኩሪ “ግብፅ ከናይል ወንዝ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳልፋ አትሰጥም” ስለማለታቸው እንዲሁ አህራም ዘግቧል።

“[ኢትዮጵያ] 630 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የዝናብ ውሃ ታገኛለች፤ 10 ወንዞቿን ሳንጠቅስ ማለት ነው። ግብጽ ግን በውሃ እጥረት አጣብቂኝ ውስጥ ወድቃለች። . . . የናይል ውሃ ጉዳይ ለግብጽ የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው።” በማለትም ተናግረዋል።

አህራም እንዳስነበበው የግብጹ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሹኩሪ ሱዳን ከግብጽ ጋር ትብብር እንድታደርግም ጥሪ ቀርቦላታል።

“ወንድማማች ህዝቦች ብቻ ስለሆንን ሳይሆን፤ የህዳሴ ግድቡ ግብጽን ብቻ ሳይሆን ሱዳንንም ይጎዳል” ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የግብጽ ፓርላማ የህዳሴ ግድብ ግንባታን የሚከታተል ልዩ ጊዜያዊ ኮሚቴ ማቋቋም ተገልጿል። ኮሚቴው የግብጽን የናይል ውሃ የመጠቀም መብት ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እንደሚያጠናም አህራም አስነብቧል።

የግብጽ ፓርላማ አባላት የሃገሪቷ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር፣ ኢትዮጵያ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ ያስከተለውን ቀውስ ለመቅረፍ የወሰደው እርምጃ እጅግ ደካማ ነው ሲሉ ስለመተቸታቸው አህራም ዘገባው ላይ አስፍሯል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ መሙላት ሂደትን በተመለከተ ለአራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ምንም ውጤት እንዳላመጣ ሳሚህ ሽኩሪ መናገራቸው ይታወሳል።