ኢትዮጵያ ሙሉ ወጪዋ በቻይና የተሸፈነ ሳተላይት ከቻይና ምድር እንደምታመጥቅ ተነገረ፡፡

ኢትዮጵያ በመጪው ታህሳስ ወር መጀመሪያ የራሷን ሳተላይት እንደምታመጥቅ ተነገረ፡፡ይህችው ሳተላይት ስለሀገሪቱ ግብርና፣ የአየር ሁኔታና የጎርፍ ተጋላጭነት ዙሪያ መረጃ የምትሰጥ ናት ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

ሙሉ ወጪዋ በቻይና መንግስት የተሸፈነው ሳተላይቷ ወደ ህዋ የምትመጥቀው ከቻይና ምድር ነው ብለዋል፡፡ዶ/ር ጌታሁን መኩሪያ ይህን የተናገሩት ዛሬ በተጀመረው 356ኛው አለም አቀፍ የአስትሮኖሚካል ህብረት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ ነው፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ ለጀመረቻቸው ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ ስራዎች ያግዛልም ብለዋል፡፡አንድ መቶ አመታት በአንድ ሰማይ ስር በሚል መጠሪያ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ከሰላሳ አገራት የተውጣጡ መቶ ስልሳ ሳይንቲስቶች እየተሳተፉበት ነው ተብሏል፡፡

አለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት ከተመሰረተ አንድ መቶ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ኢትዮጵያ ጉባኤውን ስታስተናግድ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው ተብሏል፡፡

Sheger FM