በልመና የሚተዳደሩ ሰዎች ሦስተኛ ዲግሪ ካላቸው መምህራን እኩል ገቢ ያገኛሉ

(ኢፕድ)

የአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ለልመና በተሰማሩ ሰዎች መወረራቸው ለተመልካች ግራ የሚያጋባ ነው። እነዚህ ሰዎች የልመና ስልታቸው የተለያየ ሲሆን፤ በግጥምና በዜማ ፣ ጨቅላ ሕፃናትን በመታቀፍና በማስለቀስ፣ የሰውነት አካልን የመኪና ግራሶ በመቀባት ከፍተኛ ቁስለት ያለው በማስመሰል፣ ባስ ሲልም ከዚህ ቀደም በፖሊስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እንደተጋለጠው የውሻ ቡችላ ልጅ አስመስሎ በመታቀፍና የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የሚያከናውኑት ሆኖ ይስተዋላል፡፡

በማንኛውም ዘዴ ይሁን በልመና የሚሰበስቡት ገንዘብ ሳይሰሩና ሳይለፉ የሚገኝ በመሆኑ፤ እንዲሁም የየእለት ገቢው ሲጠራቀም ዳጎስ ያለ ስለሆነ ሙሉ አካል ያላቸውና ጤናማ የሆኑ፣ ሰርተው መብላት የሚችሉ ዜጎች እጃቸውን ለልመና ዘርግተው ሳንቲም ወደ ሚያስገኘው ዘርፍ መሰማራትን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡

ለመሆኑ በርካታ ዜጎች ልመና ላይ ለምን ተሰማሩ? በቀን የሚያገኙት ገቢ ምን ያህል ነው? እነማን በልመና ላይ ተሰማሩ? ልመና የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ ምንድን ነው? የሚለውን በዝርዝር ለማወቅ በልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናቶች ተደርገዋል፡፡

በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና መምህርና በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማህበራዊ ስነልቦና የሦስተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በአዲስ አበባ በአስሩ ክፍለ ከተሞች “በጤናማ ለምኖ አዳሪዎች” ላይ እየሰሩ ያሉት አቶ አብዱሰላም ከማል፤ ስለለማኞች የገቢ መጠን ባደረጉት ጥናት ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ዶክተሮችና ሚኒስቴሮች እኩል ወርሃዊ ገቢ እደሚያገኙ ተገንዝበዋል።

አንድ ጤነኛ ለማኝ ምንም ስራ አልሰራም ከተባለ በቀን ከ100 እስከ 200 ብር ያገኛል። ይህም አንድ ለማኝ በወር ምንም አልሰራም ከተባለ ዝቅተኛ ገቢው 3ሺ ብር መሆኑን ያሳያል። ጤነኛ ለማኞች የሚያገኙት ዝቅተኛ ገቢ የመጀመሪያ ዲግሪ ካለው የመንግስት ተቋም ጀማሪ ባለሙያ ይበልጣል።

ለማኞቹ ጥሩ ሰሩ ሲባል በቀን ከ600 እስከ 700 ብር ያገኛሉ። በወር ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ገቢያቸው 12ሺ ብር ይደርሳል ማለት ነው።

መምህሩ “እኔ ሁለተኛ ዲግሪ ያለኝ የዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ። ተቆራርጦ የሚደርሰኝ ወርሃዊ ደመወዝ 8ሺ ብር አካባቢ ነው። በጥናት እንዳረጋገጥኩት በርካታ ለማኞች በደመወዝ እኔን ይበልጡኛል። ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ለማኞች ሦስተኛ ዲግሪ ካላቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን የተጣራ ወርሃዊ ገቢ ጋር የሚስተካከል ደመወዝ ያገኛሉ” ማለት ነው። ይህን ሁኔታ ማስተካካያ ካልተደረገበት በርካታ ለማኞችን ወደ ጎዳና ይጠራል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፋቸውን “በጎዳና አዳሪዎች” ላይ መሰረት በማድረግ እየሰሩ ያሉት ተመራማሪ አቶ ጥላየ ዘላለም ‹‹ ጎዳና አዳሪነት በዓለም ላይ የኑሮ ዘይቤ ሆኖ መጥቷል ፡፡ ጎዳና ተዳዳሪዎች የእራሳቸው ባህልና ወግ እየያዙ መኖር ጀምረዋል። የህይወትን ፈተናና የሚያልፉበትና የዕለት ጎርሳቸውን የሚያሟሉበት የተለያየ መንገድ አላቸው። ዋናው የህይወትን ፈተና መፍቻና መተዳደሪያቸው ግን ልመና ነው›› ይላሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳና አዳሪዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ስድስት አይነት ዋና ዋና የልመና ስልቶች እንዳሉ ያመላክታሉ። ምሁሩ እንደሚያብራሩት ገንዘብን መሰረት ያደረገ ልመና “ሽቀላ”፤ ህፃናትና ትልልቆች ለማኞችም በመንገድ ላይ እየተከተሉና እየተዟዟሩ ያለሀፍረት የሚለምኑት “ተፋጠጥ”፤ የተወሰነ ሳንቲሞችን ይዞ ጨምርልኝ እያሉ የሚያደርጉት ልመና “ፈለጣ”፤ እንዲሁም እጅን በመዘርጋት የቆሙ መኪኖችና ሰዎች መለመን “ወዲህ በሉ” ይባላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አሳዛኝ ቃላትን “ለማደሪያ፣ እርቦኛል” የመሳሰሉትን ቃላት በመጠቀምና በሀሰት ማስረጃ የሚካሄድ ልመና ለምሳሌ “ዲግሪ አለኝ ስራ የለኝም”፤ ከሆቴሎች ትርፍራፊ ምግብ የሚለምኑበት “ቡሌ”፣ አስደናቂ ቃላትን በመጠቀም ለምሳሌ “ጋሽዬ፣ አለኝታዬ፣ ሆዴን ፍቀደኝ እባክህ፤ እናቴ የአይኔ መመለሻ፤ ዛሬ ተውበሻል ባለመኪናውን ይስጥሽ ዳቦ መግዣ አባክሽ” በማለት የሚለመነው “ቅቦ” የሚባሉ የልመና ስልቶችን የሚከተሉ ሲሆኑ፤ ልመና በከተማዋና በአገር ደረጃ በእጅጉ እየተሰፋፉ መጥተዋል፡፡

መምህሩ አቶ አብዱሰላም በ2007 ዓ.ም ኤልሻዳይ የሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት በአዲስ አበባ ባደረገው ጥናት 50ሺ ለማኞች እንዳሉ ማጥናቱን፤ ከዚያ በኋላ በይፋ በጥልቀት የተካሄደ ጥናት እንደሌለ፤ ሆኖም የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባስቀመጠው ግምት በአሁኑ ወቅት ጤናማ ለማኞች ብቻ 50ሺ መድረሳቸውን፤ የጤና ችግር ያለባቸው ለማኞች ቢጨመሩ ከፍተኛ እንደሚሆንም ያመላክታሉ።

መምህሩ በጥናታቸው በዓይነታዊ በ32 እና በገላጭ 74 በድምሩ 106 ጤነኛ ለማኞች ናሙናዎች ወስደው ምርምር አድርገዋል። ባደረጉት ምርምር ዜጎች ወደ ልመና በስፋት እንዲገቡ ያደረጋቸው ምክንያቶች ልመና ምንም አይነት ብቃት አለመጠየቁ፣ ቀላልና በአጭር ጊዜ የሚለመድ ስራ መሆኑ፣ የገቢው ከፍተኛ መሆን፣ ማንም ወደ ስራው መቀላቀል መቻሉ፣ ህብረተሰቡ ጤናማና አካል ጉዳተኛውን ሳይለይ በቸርነት መስጠቱ ልመናውን ተፈላጊ አድርጎታል ይላሉ።

አቶ ጥላየ፤ በበኩላቸው ዜጎች ወደ ጎዳና የሚወጡበት ምክንያት ድህነት፣ በሞትና በፍች የቤተሰብ መለያየት፣ የወደፊቱን ህይወት አሻግሮ አለማየት፣ በቤተሰብ ውስጥ የወሲብ ጥቃት፣ የጓደኛ ግፊት፣ የዓለም አቀፋዊ ጫና፣ በአገር ውስጥ ዘርን መሰረት ያደረገ መፈናቀልና ሌሎች ምክንያቶችን መሆናቸውን ያመላክታሉ።

ለተጨማሪ https://www.press.et/Ama/?p=19814