ለአንዱ የአይሮፕላን ትኬት ሲዘጋጅ ለሌላው በቅሎ አልተዘጋጀም #ግርማ_ካሳ

አገር ቤት የሚታተመው የአገዛዙ ልሳን የሆነው አዲስ ዘመን፣ ህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም አንድ ቃለ ምልልስ አስፍሮ ነበር። ቃለ ምልልሱ የተደረገው ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች ወይም አማራዎች በገጀራ፣ በቀስት ከተገደሉበት ፣ በቅርቡም ደግሞ በመተከለ በሰላም እንዳይኖሩ በተደረገበተ የቤኔሻንጉል ክልል መስተዳደር እና ካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ሰለሞን ጂሬኛ ጋር ነበር።

በክልሉ ሌሎች ብሄረሰቦች ይፈናቀላሉ ስለሚባለው ሁኔታ እንዲያብራሩ የተጠየቁት አቶ ሰለሞን፣ የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ የሚከተለዉን ምላሽ ነበር የሰጡት፡

“የሌላ ብሄረሰብን የማፈናቀል ሴራ አለ የሚባለው አሉባልታ ነው። በተለይ ከትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር የተያያዘውን ሸርቆሌ ወረዳ አካባቢ በተወሰኑ ግለሰቦችና በነባሩ ብሄረሰብ መካከል የነበረ አለመግባባት ነበር። አለመግባባቱ እንዳይስፋፋ የክልሉ መንግስት ወደ ሥፍራው በመሄድ ከዚያ የተፈናቀሉትን በማሰባሰብ አወያይቷል። የጸጥታ አካላትን በመላክ የማረጋጋት ስራም ተከናወኗል። በከተማ መኖር የሚፈልጉ መኖር የሚችሉበትን አሰራር እና አቅጣጫ ተቀምምጧል። አብዛኛው ሰው ወደ ክልላቸው መሄድ በመፈለጋቸው የቤኔሻንግጉል ጉሙዝ ክክልል መንግስት 600 ሺህ ብር ለትግራይ ክልል ተወላጆች የአዉሮፕላን ትኬት ሸፍኖ ልኳቸዋል”

የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ የቤኒሻንጉል ክልል መንግስት፡

አንደኛ – ተፈናቃዮችን አወያይቷል።
ሁለተኛ – የጸጥታ ሃይሎችን በመላክና ሁኔታዉን በማረጋጋት የትግራይ ተወላጆች ዋስትናና ደህንነት እንዲጠበቅ አድርጓል።
ሶስተኛ፦ በክልሉ መኖር ከፈለጉ መኖር የሚችሉበት ሁኔታ አመቻችቷል።
አራተኛ – ወደ ትግራይ መመለስ የፈለግጉትን ደግሞ በአይሮፕላን ትኬት ከፍሎ በሰላም ሸኝቷል።

ለትግራይ ተወላጆች የተደረገው፣ ማንም የመንግሥት አካል ሊያደርገው የሚገባ፣ ካላደረገውና ህዝብን ለአደጋ ከሰጠ ሊጠየቅብት የሚገባ ጉዳይ ነው።

አማርኛ ተናጋሪ ወይም አማራዎች በተመለከተ ግን አቶ ሰለሞን የሚከተለዉን ነበር የመለሱት፡

“ ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ ከሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ጋር የተያያዘ ነው። ከግለሠቦች ጋር በመመሳጠር መሬትን በወረራ የመያዝና የመከለል ስራ በሰፊው ተከናውኗል። በሕግ ወጥ መንገድ የተያዘውን መሬት እንዲለቁ እና ወደ መጡበት ክልል እንዲመለሱ ተደርጓል። ከዚህም በዘለለ ግን በሕጋዊ መንገድ የመጡትን ሰዎች አይመለከተም። እንዲፈናቀሉም አልተደረገም። የሌላ ክልል ተወላጆች ሆነው ሕጋዊ መስፈርቱን አሟልተው የሚኖሩ እንዳሉም መዘንጋት የለበትም”

አማራዎች/ ወይም አማርኛ ተናጋሪዎችን በተመለከተ፣ የቤኒሻንጉል ክልል መንግስት፡

አንደኛ – ምንም አይነት ዉይይት ከተፈናቃዮች ጋር አላደረገም። አማራዎች ከሚኖሩበት ቦታ እንዲለቁ ትእዛዝ ነው የተሰጠው።
ሁለተኛ – የጸጥታ ሃይሎች አሰማርቶ በአማራው ላይ እርምጃ በመውሰድ የማፈናቀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆኗል።
ሶስተኛ – ተፈናቃዮችን ሲያፈናቅል፣ ተፈናቃዮች በሃይል፣ በጉልበት፣ በጭካኔ ነው ንብረቶቻቸውን ይዘው፣ እናቶች ልጆቻቸውን አዝለው በእግራችቸው ክልልሉን እንዲለቁ የተደረጉት። እንኳን አይሮፕላን በቅሎ አልተዘጋጀላቸውም።

ከዚህም የምንረዳቸው መሰረታዊ ነጥቦች አሉ።

የመጀመሪያው ነጥብ ኢትዮጵያዊያን ለነርሱ ዘር ከተሸነሸነው መሬት ዉጭ የመኖር ዋስተና እንደሌላቸው በግልጽ የሚያሳይ ነው። ማንኛዉም ዜጋ በማንኛዉም የአገሪቷ ክፍል በነጻነት የመኖር መብት አለው። በቤኔሻንጉል ክልል ለመኖር የሚሟላ መስፈርት መኖር አልነበረበትም። ኢትዮጵያዊነት መሆን ብቻ በቂ ነበር። በክልሉ ለመኖር የመኖሪያ ፍቃድ መጠየቅ ፣ በክልሉ ለመኖር ከጉሙዝ ወይም በርታ የሆኑ ባለስልጣናት ፋድ መጠየቅ የዜጎችን መብት መርገጥ ነው። በኬኒያ ወይንም ሱዳን ለመኖር እንደመሞከር ማለት ነው።

ሁለተኛ ነጥብ ክልሉ ለትግራይ ተወላጆች ገነት፣ ለአማርኛ ተናጋሪው ወይም አማራ ሲኦል መሆኑን ነው። ለትግራይ ተወላጆች የተደረገው እንክብካቤ አንድ አስረኛው እንኳን ለአማራው ማህበረሰብ አልተደረገም። ያ ብቻ አይደለም፣ በአማራው ተወላጆች ላይ የደረሰዉና እየደረሰ ያለው ጭካኔ እጅግ በጣም ልብ የሚሰብር ነው። የዛሬይቱ የሕወሃትና የኦህዴድ ኢትዮጵያ በየቦታው አማርኛ ተናጋሪዎች፣ አማራው፣ እንደ ጠላት እየታየ የታደነበት፣ የሚታደንበት ኢትዮጵያ ናት።

ሶስተኛውና የሚያሳዝነው ነጥብ፣ ይህ አማርኛ ተናጋሪው ማህበረሰብ ወይም አማራው ጥብቅና የሚቆምለት፣ የሚከራክርለት ድርጅት አለመኖሩ ነው። ብአዴን ዉስጡን ማጥራት ባለመቻሉ፣ አሁንም እንደነ በረከት ስሞአን ያሉትን እያግበሰበሰ በመቀጠሉ፣ ጊዜዉን የሚያጠፋው በዉስጣዊ የድርጅት ፍትጊያ ነው። የነገዱ ቡድን የበላይነቱን ቢይዝም አሁንም እንደ ጥንቸል መብረር፣ በነጻነት መንቀሳቀስ አልቻለም። እነ በረከት ወደ ኋላ እየጎተቱት ነው። በሕዝብ እንዲጠላም እያደረጉት ነው።

ከተቻለም የገዱ ቡድን አይሎ እንዲወጣ ብአዴንን መቀላቀሉ ዜጎች እንደ አማራጭ ቢያዩት ጥሩ ነው።ደህና፣ ጎበዝ፣ አገር ወዳድ ወገኖች ብአዴንን ከተቀላቀሉ እንደ በረከት ያሉ ነቀርሳዎችን በቀላሉ ከብአዴን ዉስጥ ነቅሎ መጣል ይቻላል። እነ ገዱን ማገዝ ትልቁ የትግል ስትራቴጂ ነው። ብአዴንን ጠዋትና ማታ መርገም፣ ብሶት ማሰማት ፋይዳ የለውም። ብአዴን በቶሎ ራሱን አጥርቶ እንዲወጣ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣትና መረባረብ ነው ያለብን።

በሌላ በኩል ደግሞ ለአማራው ህዝብ ቆመናል የሚሉ አንድ ሺህ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ደርጅቶች የህዝቡን ጥያቄ አንስቶ ተባብሮ ከመታገል ይልቅ በአማራነት ዙሪያ ሙግትና ክርክር ላይ ጊዜ ሲያጠፉ ነው የምናያቸው። የአማራው ክልል ህዝብ አንድ አይነት አስተሳሰብብ አይደለም ያለው። በአማራነቱ መታወቅ የማይፈልጉ፣ “ማንነታችን ኢትዮጵያዊነት ነው” የሚል አለ። “ጎንደሬ ነን፣ ጎጃሜ ነን፣ መንዜ ነን ..” የሚሉ አሉ፣ ራሳቸውን በዘር የማይለኩ። ዘር በማየት ደግሞ “አማራ ነን” የሚሉ እንዳሉት ሁሉ “ቅማንት ነን፣ አገው ነን፣ አርጎባ ነን ..” የሚሉም አሉ። እነዚህን ልዩነቶችን መቀበል ያስፈለጋል። በግድ “በአንድ ጆንያ ውስጥ ግቡ፣ አማራ ነን በሉ” ማለት ደካማነት ነው።መቆም አለበት።

በአማራነት ዙሪያ ወደፊት ካስፈለገ መጨቃጨቅ ይቻላል። አሁን ግን “ኢትዮጵይያዊ ነኝ “ አለ፤ “ አማራ ነኝ” አለ፣ “ጎንድሬ ነኝ” አለ …፣ ሁሉም አማርኛ ተናጋሪ፣ ”አማራ” ተብሎ ነው በኦሮሞ ክልል በቤኒሻንጉል…እየተገደለ፣ እየተፈናቀለ፣ እንደ መጤ እየተቆጠረ፣ እየተገፋ ያለው።

በመሆኑም የግድ ልዩነት ተወግዶ፣ በመነጋገር፣ በመስማማት በአንድ ላይ መቆም አስፈላጊ ነው። የአማራ ድርጅቶች፣ ከጎንደር ህብረት ከመሳሰሉት ጋር፣ ከአገር አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብረው መስራት መጀመር አለባቸው። በተለይም ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች መብትና ሕልዉና ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ብዙ አማርኛ ተናጋሪዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሕዝቡ የራሱ አስተዳደር ሊኖረውና በአማርኛ አገልግሎት ሊያገኝ ይገባዋል። አማርኛ ተናጋሪው ወያኔዎችና ኦነጎችን በሸነሸኑለት የአማራ ክልል ብቻ ታጥሮ እንዲኖር ተደርጎ ፣ በሌሎች ቦታዎች ግን አገር አልባ ሆኖ አንገቱ ደፍቶ፣ እየፈራና እየተሸማቀቀ መኖር የለበትም። ያንን ለማስተካከል የግድ ተደራጅቶ፣ አንድ ሆኖ፣ በውጤት ላይ ያተኮረ፣ ከስሜት የጸዳ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ብሶት ከማሰማትና ከማጉረምረም ያለፈ ትግል ማድረግ አስፈላጊ ነው።


► መረጃ ፎረም - JOIN US