መልከአ – አዲስ አበባን የመቀየር ዓመታዊ ሴራ – ፍትሕ መጽሔት

መልከአ-አዲስ አበባን የመቀየር ዓመታዊ ሴራ – ፍትሕ መጽሔት

የዘመን ድልድይን መስበር፣ ታሪክ መበረዝ፣ ትላንትን ከዛሬ መበጠስ… አገር የማፍረስ የመጀመሪያው ምዕራፍ መሆኑ ይጠቀሳል። ሕወሓት-መራሹ ኢሕአዴግ ከሩብ ክፍል ዘመን በላይ በረዘመ የሥልጣን ዕድሜው፣ አገሪቷን አልቦ-ታሪክ የማድረግ ‘ፖሊሲ’ ቀርፆ ተግብሯል፤ አስተግብሯል። አብዘሃ ማኀበረሰቦችን በወል-ማንነት ያስተሳሰሩ፣ ጥቅል ቅቡልነትን ያተረፉ ቅርሶች የሴራው ሰለባ ሆነዋል። ዘመን በተሻገሩ የከተማይቱ ምልክቶች ላይ ቡል-ዶዘር መንዳት እንደ አስተዳደር-ዘዬ ወስዷል። ልብ- ወለድ የተጫነውንና የተዛባ ትርክት ያዋቀረውን ብሔር- ተኮር ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ ወና-ከሚሞሉ ምስክሮች ገሚሱን አፍርሶ፣ ከፊሉን አዛንፎ፣ ቀሪውን አነውሯል። ይህም ኢትዮጵያውያን ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከህብረት ይልቅ ክፍለት መገለጫቸው ይሆን ዘንድ ገፍቷል።

ብረት-ነክሶ ኢሕአዴግን ለሥልጣን ያበቃው በኩር-ትውልድ ከቅርሶች በተጨማሪ፣ ነባር ሰፈሮችን በመንቀል የመዲናይቱን መስራቾች ከታሪክ-ገጽ ለመፋቅ ጀምሮት የነበረውን እኩይ ሥራ፣ ወደ ሥልጣን የመጣው ሁለተኛው ድርጅታዊው ትውልድ ከፍፃሜው ለማድረስ ቃል-የገባ መስሏል።

በርግጥም አዲስ አበባ የአምናውን ‘ለውጥ’ ተንተርሳ አስተዳደሪዋን ብትለወጥም፣ በሕግ የተመዘገቡ ቅርሶቿን ከምድረ-ገጽ የማጥፋት የ‘ጫካ ፖሊሲ’ የታደጋት አላገኘችም። ባሳለፍናቸው 12 ወራት በከተማይቱ የወደሙ ቅርሶችን በዚህ ዐውድ እንዘክራቸዋለን።

የደጃዝማች ዐምዴ-መኖሪያ ቤት

በየካ ክፍለ ከተማ ይገኝ የነበረው የደጃዝማች ዐምዴ አበራ ካሳ መኖሪያ ቤት፣ በጣውላና ጥርብ ድንጋይ የተገነባ ሲሆን፤ 7 ክፍሎች፣ 12 በሮችና 8 መስኮቶች አሉት። ከተሰራም 90 ዓመት አልፎታል። የቅርስነት መስፈርትን በማሟላቱ በክፍለ ከተማው ከሚገኙ 51 ቅርሶች መሀል አንዱ ሆኖ በመመዝገቡ መንግሥት ያውቀዋል።

ይህ የታሪክ መታወሻ እንዲፈርስ የተደረገው በያዝነው ዓመት መጋቢት ወር አጋማሽ ሲሆን፤ አፍራሹ የ‘ፌደራል ቤቶች ኮርፕሬሽን’ ነው። በወቅቱ ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢቢሲ የሰጡት የክፍለ ከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ፣ ድርጊቱ የተፈፀመው ሆን ተብሎ እንደሆነ ተናግረዋል። የተቋሙ ተወካይ ደግሞ ‘በቅርስነት ስለመመዝገቡ መረጃ የለኝም’ በሚል ተሳልቋል። መቼም መከራከሪያው እውነት ነው ቢባል እንኳ፣ ‘ሕግ አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም’ የሚለውን የጽንሰ ሃሳቡን አስተምህሮ ‘ዘነጋሁት’ ሊል አይችልም።

የደጃዝማች ዐምዴ አባት፣ ደጃዝማች አበራ ካሳ በ1928ቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ታላቅ ጀብዱ ቢፈፅሙም፣ የማታ-ማታ ከወንድማቸው አስፋወሰን ካሳ ጋር ተማርከው፣ በአንድ ቀን በስቅላት የተገደሉ አርበኛ እንደነበሩ ይታወቃል። ደጃዝማች ዐምዴ አበራም በ1966ቱ አብዮት በግፍ ከተረሸኑት 60ዎቹ ባለሥልጣናት አንዱ ናቸው።

‘ቡፌ ደ ላጋር’

‘ቡፌ ደ ላጋር (Buffet De Lagar) የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅትን አጥር ተገን አድርጎ እ.ኤ.አ ከ1924 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ ሰንብቷል። ይህ የመዝናኛ ክለብ በተለይም ለ1950ዎቹ እና 60ዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ህያው የታሪክ ምስክር እንደነበረ ይታወሳል። በወቅቱ አገሪቱ ካፈራቻቸው ዘመናዊ ባንዶች በተጨማሪ፣ ከጥላሁን ገሰሰ እስከ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የሚጠቀሱ፣ ታላላቅ ድምጻውያን የ‘ቡፌ ደ ላጋር’ መድረክን ረግጠዋል፤ ‘ማይክ’ ጨብጠዋል። በአንድ ወቅት ዓለም አቀፉ ሚዲያ BBC፣ ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ ‘‘Under African Sky’’ በሚል ርዕስ ባሰራጨው ዶክመንተሪ ፊልም፣ ‘ቡፌ ደ ላጋር’ ሰፋ ያለ ሽፋን ማግኘቱ አይዘነጋም። በፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ሰዎች ቤቱን በተመለከተና ለሙዚቃው የነበረውን አበርክቶ መስክረዋል።

‘ቡፌ ደ ላጋር’ በለገሐር አካባቢ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ውስጥ ተካትቶ ሊፈርስ መሆኑ መታወቁን ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረ/ፕ ነብዩ ባዬ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተማዋን በማልማት ዕቅድ ላይ ታሪካዊ ቦታዎችን እና ቅርሶችን ግምት ውስጥ የሚከት ዲዛይን እንደሚሰራ በአደባባይ መናገራቸውን በማስታወስ ቤቱን ከፍርሰት ለመታደግ ሦስት ገጽ ደብዳቤ ቢጽፉም ሰሚ ሳያገኙ ቀርቷል።

‘ብርሃን ለኢትዮጵያ’

‘ብርሃን ለኢትዮጵያ’ በወ/ሮ ሳቤላ በላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ‘ቡልጋሪያ’ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የሚገኝ ሙዚየም መሰል አወቃቀር ያለው መኖሪያ ቤት ነው።

‘ብርሃን ለኢትዮጵያ’ ከመግቢያው በርና የድንጋይ አጥር ጀምሮ እያንዳንዱ ክፍል፣ ግድግዳ፣ መስኮት፣ በር፣ የአትክልት ቦታው… ኢትዮጵያን በሚወክሉ የታሪክ ማስታወሻዎች የተበጀ ነው። በተጠቀሰው ክፍለ ከተማ ቀበሌ 05 የሚገኘው ይህ ቪላ በአካባቢው ከተሰሩ ቀዳሚው ሲሆን፤ የቤት ቁጥሩም 001 ነው።

ለረጅም ዓመት የዓድዋን ድል በሚያጎሉ ተግባራት ላይ ይሳተፉ የነበሩት ወ/ሮ ሳቤላ፣ ቤቱ ከአንዲት አገር ወዳድ ዜጋ በስጦታ ከተበረከተላቸው ጀምሮ፣ ትንሿን ኢትዮጵያ እንዲወክል የማድረግ ህልማቸውን ለማሳካት ፕሮጀክት ቀርፀው ተግብረዋል። በ2003 ዓ.ም. እና በ2008 ዓ.ም ከአዲስ አበበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ከፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ የተወጣጡ ባለሙያዎች ሁለት ጊዜ በቅርስነት መዝግበውታል።

ይህ በግለሰብ አንጡራ ሀብትና ጥረት የተመሰረተው ሙዚየም፣ በያዝነው ዓመት ወርሃ ሰኔ ‘ለመንገድ ሥራ’ በሚል ሰበብ፣ የሐረር እና ፋሲለደስ ግንቦችን እንዲወክሉ ተደርገው የተሰሩትን ጨምሮ፣ በ17 ብሔረሰቦች ባህላዊ ጎጆዎች እና በዶርዜ ኪነ-ጥበብ አምሳያ የተቀረፁ ቅርሶች ሙሉ በሙሉ እንዲፈርሱ ተደርጓል። ድርጊቱን አስደንጋጭ የሚያደርገው የፍርድ ቤት እግድ ተጥሶ መፈፀሙ ነው።

የራስ አበበ አረጋይ ቤት

በአዋሬ አካባቢ ዓድዋ መንገድ የሚገኘው የዝነኛው አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ታሪካዊ መኖሪያ ቤት ከተሰራ ከ70 ዓመት በላይ አስቆጥሯል። ባህልና ቱሪዝም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ‘ታሪካዊ ቤቶች’ ብሎ ከያዛቸው ከ400 በላይ ቅርሶች አንዱ ነው።

ቤቱን ታዋቂው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ገዝቶት የነበረ ቢሆንም፣ ለ‘አክሰስ ሪል ስቴት’ መልሶ ሸጦታል። አክሰስ ደግሞ ዛሬ ቅርሱን ላወደመው ‘ሙለር ሪል ስቴት’ በ4 ሚሊዮን ብር ሽያጭ አስተላልፎታል።

በወቅቱ መኖሪያ ቤቱ እየፈረስ እንደሆነ ጥቆማ የደረሰው ባህልና ቱሪዝም ድርጊቱ እንዲቆም የሚያሳስብ ደብዳቤ ለድርጅቱ ቢጽፍም፣ ከፍርሰት ሊታደገው አልቻለም። በሌላ በኩል የ‘ሙለር ሪል ስቴት’ መስራች አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ፣ ቤቱ ከታሪካዊ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንደማይገኝ ተነግሯቸው እንደነበረ በመጥቀስ ሲከራከሩ ተደምጧል። ራስ አበበ አረጋይ በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መከላከያ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ በ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾች መገደላቸው ይታወቃል።

ሌላው በ‘ማስፋፊያ’-ስም አደጋ የተጋረጠበት ድሮ ‘ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት’፣ አሁን ‘ብሔራዊ ቲያትር’ ተብሎ የሚታወቀው ታሪካዊ አዳራሽነው። በ1948 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነባው ይህ ቲያትር ቤት፣ ለመድረክ ትዕይንቶችም ሆነ ለተመልካች እጅግ ምቹ ተደርጎ በተዋበ ሥነ-ሕንፃ ጥበብ የታነፀ ነው። በአሁኑ ወቅት ምንም ዐይነት ክትትልና እንክብካቤ ስለአልተደረገለት የተወሰኑ ወንበሮቹና አንዳንድ መሰረተ-ልማቶቹ እርጅና ከጥቅም ውጪ አድርጓቸዋል።

መንግሥት ስድስት አስርታት ያስቆጠረውንና ከከተማይቱ ዋንኛ የኩራት መገለጫዎች አንዱ የሆነውን ‘ብሔራዊ ቲያትር ቤት’ን በማስፋፋት ስም፣ ታሪካዊ ቅርስነቱን የሚያዛንፍ፣ የሥነ-ሕንፃ ዲዛይኑን የሚከልስ ድርጊት እንዳይፈጽም ታላቅ ጥንቃቄ ያደርግ ዘንድ ከወዲሁ ይመከራል። ‘ብሔራዊ ቲያትር ቤት’ የሚያስፈልገው ዕድሳት፣ ጥገናና ክትትል እንጂ፣ የማስፋፊያ ፕሮጀከት አለመሆኑንም ማስታወሱ ተገቢ ነው። ይህን ጉዳይ አሳሳቢ ያደርገው የአገሪቱ የመጀመሪያ በሆኑት ዳግማዊ ምንሊክ ተፈሪ መኮንን እና እቴጌ መነን ትምህርት ቤቶች ላይ እየተደረገ ያለው ዕድሳት የፈጠረው ማዛባት ነው። ምንም እንኳ ወደ ግንባታው ከመገባቱ በፊት ቅርስና አስተዳደር የባለሙያ ድጋፍ እንዲያደርግ በደብዳቤ የተጠየቀ ቢሆንም፣ በዕድሳቱ ላይ የተቋሙ ምክረ-ሃሳብ እንዳልተተገበረ ‘ፍትሕ’ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በፒያሳ ጊዮርጊስ (አራዳ) ሜዳ፣ የዓድዋ ጀግኖችን የሚዘክር ማዕከል ለማቋቋም ከስድስት ወር በፊት ቃል በመግባቱ እያመሰገንን፣ ወደ ተግባር ይቀይር ዘንድ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚጠበቅበት ለማስታወስ እንወዳለን።

መንግሥት እንዳሻው የሚፈነጭበት ሥልጣን አገራዊ ቅርሶችን በጀት መድቦ መጠበቅ፣ ችግር የገጠመውን ደግሞ ማደስን የሚጨምር መሆኑን ዘንግቶታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡት ጥንታዊያኖቹ የአክሱም ሃውልት እና የቅዱስ ላሊ-በላ ቤተ-ክርስቲያናት ሳይቀሩ ለአደጋ ተጋርጠው ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ነገር አለመደረጉ መሬት የረገጠ እውነታ ነው። ከወራት በፊት የላሊ-በላ አብያተ- ክርስቲናትን የጎበኙት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማንኤል ማክሮን ለዕድሳት የሚውል 200 ሚሊዮን ዩሮ ለመለገስ ቃል-እንደገቡ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አንደበት ጭምር የተነገረ ቢሆንም፣ ዛሬ ድረስ የተደረገ ነገር እንደሌለ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ሁነቱ ‘ኢትዮጵያዊነትን አጠፋለሁ’ በሚል ከንቱ ምኞት አያሌ ቅርሶችን ያወደመው፣ ሃውልት ነቅሎ የወሰደው ጣሊያን ከተባረረ 76 ዓመት ቢያልፈውም፣ ዕኩይ-ግብሩ ዜግነት ቀይሮ እዚሁ መቅረቱን ያስረግጣል።