በወቅቱ ክፍያ የማይፈጽሙ የውኃ ተጠቃሚዎች መንግስት ወለድ ሊያስከፍላቸው ነው

አዲስ በተጀመረው የባንክ ክፍያ ሥርዓት ከ265 ሺሕ በላይ ደንበኞች ክፍያ አልፈጸሙም

የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የውኃ አገልግሎት ክፍያቸውን በወቅቱ የማይከፍሉ ደንበኞቹን የውኃ መስመር ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን፣ የመክፈያ ቀኑ ካለፈበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ የባንክ ወለድ (በሕግ በተቀመጠው የወለድ መጠን) ለማስከፈል መወሰኑንና በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚያደርገው አስታወቀ፡፡

ከ566,000 በላይ ደንበኞች እንዳሉት የሚናገረው ባለሥልጣኑ፣ ወለድ የሚያስከፍለው በሕግ አስገዳጅነት ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ ወጪዎችንም እንደሚያካትትና የቆጣሪ ማስቀጠያም 480 ብር እንደሚያስከፍልም አስታውቋል፡፡

የባለሥልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው ዓርብ መስከረም 9 ቀን 2012 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣  ባለሥልጣኑ የውኃ ፍጆታ ክፍያን በተለያዩ መንገድ ሲሰበሰብ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡ ከሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መሰብሰብ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ የውኃ ፍጆታ መጠንን ለማወቅ ቤት ለቤት እየተዞረ ቆጣሪ በማንበብ ይከናወን የነበረውን አሠራር ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ በውኃ ፍጆታ ቅድመ ክፍያ ቴክኖሎጂ መተካቱን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የሚደረገው ክፍያ በሲቢኢ ብር (CBE Birr)፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ በሚመቻቸው ቅርንጫፍ በአካል ተገኝቶ መክፈል እንደሚቻል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን አራት አማራጮች መጠቀም ለማይችሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የተለያዩ አካላት ልዩ የሒሳብ ቁጥር (Ear marked Account) መዘጋጀቱንም አቶ ሞገስ ገልጸዋል፡፡

ደንበኞቹ ክፍያ ለመፈጸም ወደ ባንክ ሲሄዱ የመለያ ቁጥራቸውን ማወቅና መያዝ እንዳለባቸው፣ በየወሩ የሚፈለግባቸውን የውኃ ሒሳብ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የባለሥልጣኑን ድረ ገጽ በመጠቀም ማወቅ እንደሚችሉም አክለዋል፡፡ ለሚከፍሉት ክፍያ ማረጋገጫ ደረሰኝ ማግኘት እንዳለባቸውና ዝም ብለው ገንዘብ አስገብተው ብቻ መሄድ እንደሌለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ ደንበኞች የተጠቀሙበትን የውኃ ፍጆታ ክፍያ በወቅቱ አለመፈጸም በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ካሉት 566,000 ደንበኞች ውስጥ 265,887 ደንበኞቹ በባንክ ክፍያ ከተጀመረ ከሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. አለመክፈላቸውን ጠቁመው፣ በገንዘብ ሲሰላ 136,381,453 ብር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ደንበኞች ውስጥ 3,243 የሚሆኑት ዋና ደንበኞች የሚባሉት የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ ሆቴሎችና በኮንዶሚኒየም ቤት የሚኖሩ ደንበኞች መሆናቸውንና በገንዘብ ሲሰላ ከ81 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ከ200,000 በላይ የሚሆኑ የኮንዶሚኒየም ቤት ደንበኞች ከስድስት ወራት በላይ ክፍያ ያልፈጸሙ መሆናቸውንና ቆጣሪ ማንሳት ሊጀመር መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በመግለጫው ላይ የተገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተለይ የውኃ አቅርቦትንና ሥርጭትን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ቢሆንም ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹የእኔ ኃላፊነት ከደንበኞች አገልግሎት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ሥርጭትና አቅርቦት የሚመለከተው ሌላ ዘርፍ ነው፡፡ በቅርቡ መግለጫ ይሰጣል፤›› በማለት የተሟላ መረጃ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡