ለአራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የአባይ ግድብ የሦስትዮሽ ውይይት ምንም ውጤት እንዳላመጣ ግብፅ ተናገረች

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ መሙላት ሂደትን በተመለከተ ለአራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይት ምንም ውጤት እንዳላመጣ የግብጹ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹህሪ ተናገሩ።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ካይሮ ውስጥ ከኬኒያዋ አቻቸው ሞኒካ ጁማ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።

ሳሚህ ሹህሪ እንዳሉት ሃገራቸው ከአባይ የምታገኘውን የውሃ ድርሻን በከፍተኛ ደረጃ እስካልቀነሰው ድረስ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ያላትን መብት ግብጽ እውቅና እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግዙፍ ግድብ 6 ሺህ ሜጋዋት የሚደርስ የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ እንደተጀመረ ይታወሳል። ግብጽም ከወንዙ የማገኘውን የውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል የግድቡን ግንባታ በቅርብ ስትከታተል ቆይታለች።

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ሱዳንና ግብጽ የሚሳተፉበት የሦስትዮሽ ውይይት በግድቡ ዙሪያ ሲካሄድ ቆይቷል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ደግሞ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት የጀመረችው ሃገራቸው እ.አ.አ. በ2011 የገባችበትን ቀውስ ተከትሎ መሆኑን ‘አህራም ኦንላየን’ ከተባለው የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

”ግብጽ በዛ ወቅት አለመረጋጋት ውስጥ ባትሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ መገንባት አትጀምርም ነበር” ብለዋል።

”ከ2011 ግርግር ግብጻውያን ብዙ መማር ያለባቸው ነገሮች አሉ። ይህንን ትልቅ ሃገራዊ ስህተት ልንደግመው አይገባም” ሲሉም ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በግብጽ የተከሰተውን ህዝባዊ አብዮት ተከትላ ግድቡን መገንባት ለአመጀመሯን ይናገራሉ። ኢንጅነር ክፍሌ እንደሚሉት ምንም እንኳ ይፋዊ የግድብ ግንባታው መጀመር ምርቃት የተደረገው እአአ 2011 ላይ ቢሆንም ግንባታው የተጀመረው የፈረንጆቹ 2010 ዓመት መጨረሻ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያያዘ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የግብጽ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ የውሃ ሚኒስትሮች የሚያድርጉት ውይይት ትናንት በካይሮ እንደተጀመረ አስታውቋል።

ውይይቱ ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ በአዲስ አበባ ተካሂዶ ከነበረው ስብሰባ የቀጠለ እንደሆነ ታውቋል።

የውሃ፣ መስኖና ሃይል ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በጥሩ መንፈስና እና በመተባበር ላይ መሰረት ያደረገ ስራ ስታከናውን እንደቆየች ገልጸዋል።

በሶስቱ ሃገራት መካከል በጉዳዩ ላይ የሚደረሰው መግባባት የሁሉም ሀገራትን ጥቅም ለማስከበር ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የካይሮው ውይይት ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው ሀገራቱ በቀሪ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በባለሙያዎች የቀረበለትን ሪፖርት እና ምክረ-ሃሳቦች መርምሮ የወደፊት መመሪያዎችን ለማበጀት መሆኑ ተጠቁሟል።

ሀገራቸውን ወክለው በውይይቱ የተገኙት የግብጹ የውሃ ሚኒስትር ዶክተር ሞሐመድ አብድል አቲ ደግሞ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየታየ ያለው የትብብር መንፈስ ለሌሎች ሀገራትም አርአያ ይሆናል ብለዋል።

በግድቡ አሞላል እና የውሃ አለቃቀቅ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች የሶስቱንም ሃገራት ጥቅም መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሱዳኑ የውሃ እና መስኖ ሚኒሰትር ፕሮፌሰር ያሲር ሞሐመድ አባስ ሃገራቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የጀመሩት ትብብር ስኬታማ ስራዎች የተከናወኑበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።