በአፋር ዳሎል የጠፋቸው እስራኤላዊት ተማሪ ህይወቷ አልፎ ተገኘች

DW

በአፋር ክልል ዳሎል አካባቢ ለጉብኝት ከሄዱ እስራኤላውያን ተማሪዎች መካከል ተነጥላ ጠፍታ የነበረችው እስራኤላዊት ወጣት ዛሬ ጠዋት ሞታ ተገኘች።

አያ ናማና የተሰኘችው ወጣት አስክሬን ዛሬ ከሰዓት ወደ አምቡላንስ መወሰዱን አንድ የአፋር ክልል ባለስልጣን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ የቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ አህመድ አብዱልቃድር እስራኤላዊቷ መጥፋቷ ከታወቀበት ከትላንት ጀምሮ ሊሊቱን ሙሉ ፍለጋ ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።

ለሊቱን ሙሉ ሲደረግ በነበረው ፍለጋ የክልሉ መንግስት ኃላፊዎች፣ የበረሃሌ ወረዳ ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንደዚሁም የአካባቢው ነዋሪዎች መሳተፋቸውን አስረድተዋል። የወጣቱ አስክሬን በአካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ ጠዋት መገኘቱንም አክለዋል። Entführung Touristen Äthiopien (picture-alliance/dpa)

“ሬሳው ዛሬ ጠዋት ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው የተገኘው። እዚያ አካባቢ ጸሀይ በጠዋት ስለምትወጣ የአካባቢ ነዋሪዎች ከለሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ነው [ለፍለጋ የወጡት]። ከመቶ በላይ ሰው ነው ዛሬ ለፍለጋ የተሰማራው። ‘ድሮን’ም ነበር። እነዚያ ሰዎች እስከ ሶስት ሰዓት እየፈለጉ ነበር። ወደ መመለሻው ሳይሆን ወደ ፊት፣ ወደ አንድ ኪሎ ሜትር ሄዳ ነው የተገኘችው። ሬሳዋ እዚያ ነው የተገኘው። እስከ አራት ሰዓት ተኩል ድረስ እዚያው ነበሩ ከዚያ በኋላ ሬሳው የሚነሳበት መሳሪያ መጥቶ፣ አንስተው በአምቡላንስ ወደ መቀለ ነው የላክነው። አውሮፕላን በአቅራቢያው እዚያ ስለሆነ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እስራዊላዊቷ ወጣት ሞታ የተገኘችበት ዳሎል የተሰኘው ቦታ ከባህር ጠለል በታች 116 ሜትር የሚወርድ ሞቃታማ ቦታ ነው። በአካባቢው ባለው እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሚደርሰው ከፍተኛ ሙቀት የተነሳ ወደ አካባቢው የሚመጡ የአገር ጎብኚዎች በጠዋት ጉብኝታቸውን እንዲያጠናቅቁ እንደሚደረግ አቶ አህመድ ይገልጻሉ። የትላንትናው ክስተት እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ እንዲህ አስረድተዋል።

“ትላንትናም በቡድን የመጡ ቱሪስቶች ነበሩ። ከእነዚህ ቱሪስቶች ውስጥ አምስት ከእስራኤል የመጡ ነበሩ። እነዚህ ቡድኖች ወደ ጉብኝቱ ቦታ በተለያየ አስጎብኚ ድርጅቶች በአንድ ላይ ሰብስበዋቸው ነው የመጡት። መኪና ከሚቆምበት ፖታሽ የሚታይበት ትንሽ ዳገትማ፣ ተራራማ ነገር አለው። ፎቶ ለመነሳት ቦታው እየመረጡ ሁሉም በየፊናው እየሄደ ይነሳ እና ነው የሚመለሰው። በመመለሻቸው ጊዜ እርሷን ያጧታል፤ አልተመለሰችም። ከዚያ በኋላ እርሷ እንደቀረች ቡድኑ ሪፖርት ያይና ለፍለጋ ይመለሳሉ።

እርሷ ከዚያ ከሚጎበኘው ቦታ አንድ ኪሎ ሜትር ያህ ሄዳ ነበርና ወደዚያ መንገዱም ጠፍቷት ነው ያልተመለሰችው። ድካምም የሚሰማበት፣ አንዳንዴ እግርም የሚሰምጥበት ጊዜ አለና መንገድ ጠፍቷት ነው። ትክክለኛ የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ ከሬሳ ምርመራ በኋላ ነው የሚታወቀው የጤንነት ችግር ከሌለባት በስተቀር በውኃ ጥም እንደሞተች ነው እኛ ያገኘነው ብለዋል” ሲሉ ምክትል የቢሮ ኃላፊው ክስተቱን አብራርተዋል።

የእስራኤላዊቷ ተማሪ ሞት ለቤተሰቦችዋ እንደተነገረ የእስራኤል ጋዜጣ ጀሩሳሌም ፖስት ዘግቧል። የእስራኤል ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የተማሪዋን አስክሬን ወደ ሀገርዋ ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጋዜጣው አክሎ ገልጿል።