በኤርትራና በትግራይ ክልል ያሉ እስረኞች የማይፈቱበት ምክንያቱ ምንድነው ??? (ምንሊክ ሳልሳዊ )

በኤርትራና በትግራይ ክልል ያሉ እስረኞች የማይፈቱበት ምክንያቱ ምንድነው ??? (ምንሊክ ሳልሳዊ )

በኤርትራና በትግራይ ክልል ያሉ እስረኞችን አስመልክቶ ዝምታው መፈንዳት አለበት። የማይፈቱበት ምክንያቱ ምንድነው ??? እርስ በእርስ በብሔርና በቋንቋ ከምንፋጅ ከምንጠላለፍ ከምንፈራረጅ ለወገኖቻችን ቅድሚያ እንስጥ።

የወገን ጉዳይ የሚጨንቃቸው አልፎ አልፎ እንዲሁም የፖለቲካ ፍጆታቸውን ለመሙላት የሚጥሩት እንደለመዱት በኤርትራና በትግራይ ክልል የታሰሩ ዜጎችን አስመልክቶ በየፊናቸው የራሳቸውን ሲናገሩ እንሰማለን ፤ ለወገን የሚጨነቀው ይፈቱ ብሎ ሲጮህ የፖለቲካ ፍጆታው እንዳይጎልበት የሚራወጠው ደግሞ አስረኞቹ እንደተፈቱ የማስመሰል ፕሮፓጋንዳውን ሲረጭ ሰምተናል።

በኤርትራ ከደርግ ዘመን ጀምሮ የታሰሩ እንዲሁም ከትግራይ ታፍነው የተወሰዱ ሲልም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኤርትራ ገብተው የታሰሩ በባድመ ጦርነት ምርኮም የታሰሩ በሺዎች የሚቆተሩ አስረኞች ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የታሰሩም ይሁኑ የሞቱ ምርኮኞችን በሕግ አግባብ መሰረት ማስረከቧ ሲታወቅ የ ኤርትራ መንግስት ግን አንድም የታሰረ ይሁን የሞተ ኢትዮጵያዊ አላስረከበም። በዓለም ዓቀፍ የምርኮኞች ሕግ መሰረት መፈጸም የሚገባውን የሕግ አግባብ አልፈጸመም። የ ኤርትራ መንግስት በተለያዩ መንገዶች ይዞ ያሰራቸውን ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ሊፈታ ይገባል። ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች በጉልበት ስራ ላይ ተሰማርተዋል የሚሉ መረጃዎች ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ ተሰምተዋል።

ወደ ራሳችን አገር ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ በትግራይ ውስጥ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ታፍነው የተወሰዱ በተለይ ከኦሮሚያና አማራ ክልል ታፍነው ሳይፈረድባቸው በትግራይ እስር ቤቶች የሚገኙ ከሁለት ሺህ በላይ አስረኞች እንዳሉ ይታወቃል። በቅርቡ ከሽሬ ወታደራዊ ካምፕ የምድር ቤት አስር ቤቶች የተፈቱት የኦሮሞና አማራ ወጣቶች የሰጡት መረጃ እንደሚያሳየው ቀጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የፍትሕ አካል ሳይዳኛቸው ታፍነው ተወስደው መታሰራቸውን ተናግረዋል ። እንዲሁም በመቀሌ አዲግራት አድዋና አክሱም በሚገኙ ሰፋፊ የማሰቃያ አስር ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በስቃይ ላይ መሆናቸውን በየእስር ቤቶቹ አፈትልከው የሚወጡ የደብዳቤ ማስረጃዎች በገሃድ ይመሰክራሉ። ይህ ሁሉ ግፍ በወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽሙ የሕወሓት ባለስልጣናት በአስቸኳይ ካለሕግ ትእዛዝ የታሰሩትን በሙሉ ሊፈቷቸው ይገባል።

የሻእቢያና የሕወሓት ባለስልጣናት በተመሳሳይ ባሕሪያቸው ተሰንገው ኢትዮጵያውያንን በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ። ወገን ለወገን ደራሽ መሆኑን የምናረጋግጠው እስረኞቹ ስለኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ብለው የታሰሩ ስለሆን እንዲፈቱ ሁላችንም ድምጻችንን ልናሰማላቸው ይገባል።የማይፈቱበት ምክንያቱ ምንድነው ??? የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ዘብ በመቆም ሊያስፈታቸው ይገባል። #MinilikSalsawi