የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን እስረኛ ኢትዮጵያውያንን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ለቀቃቸው

BBC Amharic : ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ጂፒ በተሰኘው የንግድ አካባቢ ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ታስረው ከነበሩ 150 ኢትዮጵያውያን ከ140 በላይ የሚሆኑት እስከ ትናንት ምሽት ድረስ መለቀቃቸው ተነገረ።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ለቢቢሲ ሲናገሩ ታስረው የነበሩት ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ፍቃድ እንዳላቸው ከተረጋገጠ በኋላ እንደተፈቱ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ 450 የሚሆኑት እስረኞች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን ባላቸው መረጃ ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል ኢትዮጵያዊያን እንዳልነበሩ አምባሳደሩ ገልፀዋል።

አምባሳደሩ ጨምረው እንደተናገሩት አሁን በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውንን በተመለከተ ኤምባሲው አስፈላጊውን ማጣራት እና ከሚመለከታቸው የሃገሪቱ ሃላፊዎች ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ፖሊስ ኢትዮጵያዊያኑን ያሰራቸው ተመሳሳይ ተደርገው የተሰሩ ሃሰተኛ ምርቶችን ይሸጣሉ በሚል ጥርጣሬ ነበር።

ተመሳሳይ ያልሆኑና በፖሊስ የተወሰዱ የኢትዮጵያዊያኑን እቃዎች ለማስመለስ ኢትዮጵያዊያኑ ጠበቃ ቀጥረው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱትና ኤምባሲውም ለዚህ ድጋፍ እንደሚያደርግ አምባሳደሩ አመልክተዋል።

ከቀናት በፊት ጂፒ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሬስቶራንት ባለቤት የሆነው አቶ ተከስተ ሹምዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ህገወጥና ሐሰተኛ ምርቶችን እንቆጣጠራለ በሚል ምክንያት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጎ ነበር።

በወቅቱ ፖሊስ በአካባቢው የተገኙ ግለሰቦች ያለምንም ማጣራት ወደ እስር ቤት መውሰዱን የአይን እማኞች የገለጹ ሲሆን፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች የመኖሪያ እና የንግድ ፍቃድ እንዳላቸው እንዲሁም ከሳምንት በፊት በተከሰተ ግጭት በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ያልተሳተፉ መሆናቸው ተጣርቶ እንደሚፈቱ ፖሊስ ማስታወቁን አቶ ተከስተ ነግረውናል።

“የሃገሪቱ ባለስልጣናት በሚቻለው ፍጥነት አስፈላጊ ማጣራቶችን አድርገው እንደሚለቋቸው፤ እስከዚያው ግን በህክምናም ሆነ የምግብ ፍላጎታቸው እንደሚሟላ ቃል ገብተውልን ነበር” የሚሉት አምባሳደር ሽፈራው (ዶ/ር) ናቸው።

አምባሳደሩ እንደሚሉት ከሆነ ቀድሞውን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርገው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 150 ነበር።


► መረጃ ፎረም - JOIN US