በህዋ ላይ እየተንቀሳቀሰች መረጃዎችን የምትሰበስበው ዓለም አቀፍ የህዋ ጣቢያ ዛሬ ምሽት በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ እንደምታቋርጥ ተነገረ።

BBC Amharic : በህዋ ላይ እየተንቀሳቀሰች መረጃዎችን የምትሰበስበው ዓለም አቀፍ የህዋ ጣቢያ ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ከ52 ደቂቃ ሲሆን በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ እንደምታቋርጥ ተነገረ።

ዛሬ ነሐሴ 06/2011 ዓ.ም ምሽት 1 ሰዓት 52 ላይ ሲሆን በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ የምትታይ ሲሆን የአየሩ ሁኔታ ደመናማ ሆኖ ካልጋረዳት በስተቀር፤ አመቺ ቦታ ላይ ከተሆነ ያለምንም መሳሪያ እገዛ በዓይን ልትታይ እንደምትችል ተገልጿል።

ዓለም አቀፏ የህዋ ጣቢያ በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ ስታቋርጥ ልትታይ የምትችለው ለስድስት ደቂቃዎች ያህል እንደሆነም ተገልጿል።

የህዋ ጣቢያዋ ምን ታደርጋለች?

የህዋ ጣቢያዋ ከመሬት ስበት ውጪ ሆና በምድር ዙሪያ የምትሽከረከር ናት። አንድ የእግር ኳስ ሜዳን የምታክለው ጣቢያዋ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምሮችና ሙከራዎች ያለማቋረጥ በውስጧ ባሉ ባለሙያዎችና በእራሷ አማካይነት ታደርጋለች።

በምድር ዙሪያ በምትንሳፈፈው በዚች የህዋ የሙከራ ጣቢያ ምድር ላይ ላለው የሰው ልጅ ጠቀሜታ ያላቸው ምርምሮችን ከማድረግ በተጨማሪ ለወደፊቱ የህዋ አሰሳ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ትሰበስባለች።

መቼ ነው የምትታየው?

ይህች የህዋ ጣቢያ ደመና ካላጋረዳት በስተቀር እንደ ጨረቃ የፀሐይን ብርሐን ስለምታንጸባርቅ ያለምንም መሳሪያ መመልከት ይቻላል። ነገር ግን ይህችን የህዋ ጣቢያ የቀን ብርሃን ባለበት ጊዜ ለመመልከት አስቸጋሪ ነው።

በተለይ የፀሐይ ብርሐን በሌለበት ጊዜ ከመንጋቱ በፊትና ምሽት ላይ በደንብ ማየት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የህዋ ጣቢያዋ ምን ትመስላለች?

የህዋ ጣቢያዋ ግዙፍ አውሮፕላን ወይም እጅግ ደማቅ በሰማይ ላይ የምትንሳፈፍ ኮከብ የምትመስል ስትሆን ብልጭ የሚል ብርሃን የላትም። እንዲሁም የጉዞ መስመሯን ሳትቀይር በአንድ አቅጣጫ የምትጓዝ ናት። የመንቀሳቀስ ሁኔታዋም አንድ አውሮፕላን ከሚጓዝበት ፍጥነት እጅግ በበለጠ ሁኔታ በሰማይ ላይ ትጓዛለች።

የህዋ ጣቢያዋ በምን ያህል ፍጥነት ትጓዛለች?

ዓለም አቀፏ የህዋ ጣቢያ 28 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በሰዓት በመጓዝ በየዘጠና ደቂቃው ዓለምን ትዞራለች። በዚህም በጣቢያዋ ውስጥ ያሉ ጠፈርተኞች በየዕለቱ ፀሐይ 16 ጊዜ ስትጠልቅና ስትወጣ የማየት ዕድል አላቸው።

የህዋ ጣቢያዋ በጨለማ እንዴት ልትታይ ትችላለች?

ደመናማ የአየር ሁኔታ ካልጋረዳት በስተቀር የህዋ ጣቢያዋ ልክ እንደ ጨረቃ ከፀሐይ የምታገኘውን ብርሐን ስለምታንጸባርቅ በደንብ ትታያለች።

በምሽት ጨረቃ ባትታይ እንኳን የህዋ ጣቢያዋን ለመመልከት ምንም አዳጋች ሁኔታ አይፈጠርም።


► መረጃ ፎረም - JOIN US