በደቡብ ክልል ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል አምስት ሰዎች ቆሰሉ

DW : በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ትናንት ምሽት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች አምስት ሰዎች ላይ መቁሰላቸውን የወረዳው ባለስልጣን አሰታወቁ።

በተለምዶ ባጃጅ ተብሎ በሚጠራ ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው የአማሮ ወረዳን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ከሚያዋስነው ኮምቦልቻ በተባለ የገጠር መንደር ውስጥ ነው። ጥቃቱ በተሽከርካሪው ላይ በነበሩ ስድስት ሰዎች ላይ መፈጸሙን የተናገሩት የአማሮ ወረዳ የባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ተወካይ አቶ አማረ አክሊሉ «የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል፣ ሁለቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል» ሲሉ ተናግረዋል።

ስለ ጥቃቱ ፈፃሚዎችም ሆነ ስለ ጥቃቱ መንስኤ የታወቀ ነገር የለም። በአካባቢው ባለፈው አንድ አመት በተፈጸሙ ጥቃቶች እና በተቀሰቀሱ ግጭቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US