በግል ትምህርት ቤቶች እየተደረገ ያለው የክፍያ ጭማሪ ወላጆችን እያማረረ ነው

EPA : አዲስ አበባ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች እየተደረገ ያለው የክፍያ ጭማሪ በወላጆችና ትምህርት ቤቶች አስተዳደር መካከል ውዝግብ እየፈጠረ ይገኛል።

አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንደተናገሩት የግል ትምህርት ቤቶቹ የአገሪቱን የኢኮኖሚም ሆነ የወላጆችን የመክፈል አቅም ያላገናዘበና የተጋነነ ክፍያ በመጠየቃቸው ምክንያት በመጪው 2012 ዓ.ም ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር መቸገራቸውን ገልፀዋል።

የሳፋሪ አካዳሚ የወላጅ ኮሚቴ ፀሀፊ አቶ መንግስቱ ታደሰ እንደተናገሩት የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ከወላጅ ኮሚቴ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ የተጋነነ የክፍያ ጭማሪ አድርጓል። ጭማሪው የተጋነነ መሆኑን በተመለከተ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ባቀረበው “ጥናት” (ፕሮፖዛል) ላይ ተደጋጋሚ ውይይት ቢደረግም፤ የወላጆች አስተያየት በአስተዳደሩ በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም።

አቶ መንግስቱ እንደተናገሩት የተደረገው ጭማሪ ተገቢነት የሌለው፣ የተጋነነ፣ ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀምሌ 30/2007 ዓ.ም ያወጣውን መመሪያ በተለይም “የተከለከሉ የክፍያ አይነቶች” (አንቀፅ 8) በሚለው ስር ምንም አይነት ክፍያ ለአጋዥ መፃህፍት፣ ለኮምፒዩተርና ለሌሎች አገልግሎቶች ተጨማሪ ክፍያ አይፈፅሙም የሚለውን የጣሰ ነው።

ይህንኑ በተመለከተም እንደ ወላጅ ኮሚቴም ሆነ ወላጅ፤ ከግንቦት ወር ጀምሮ እንዲስተካከል ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ በትምህርት ቤቱ ሶስት ቅርንጫፍ ያሉ ወላጆችም የጋራ ውይይት አድርገው 850 ወላጆች ፊርማቸውን በማኖር ጭማሪውን መቶ በመቶ ቢቃወሙትም አስተዳደሩ ምንም አይነት ማስተካከያ ሊያደርግ አልቻለም።

የወላጅ ኮሚቴው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር መጨመር እንደሚችል፤ ነገር ግን ጭማሪው የተጋነነ መሆን እንደሌለበት ሀሳብ ቢያቀርብም በትምህርት ቤቱ አስተዳደር በኩል ግን ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም ያሉት አቶ መንግስቱ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ቢያቀርቡም ምላሽ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ምን ያህል እንደተጨመረ የጠየቅናቸው አቶ መንግስቱ ከ1-4ኛ ክፍል 1ሺህ 260 የነበረው ክፍያ 59 በመቶ በመጨመር 2ሺህ ብር፤ ከ5-8ኛ 1ሺህ 252 በነበረው ላይ 60 በመቶ በመጨመር ብር 2ሺህ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ትምህርት ቤቱ ያለ ምንም አይነት ደረሰኝ ለተማሪዎች ምረቃ፣ የአጋዥ መፃህፍት ግዥ እና የመሳሰሉትን እንደሚሰበስብም ተናግረዋል።

በመንግስት የተሰጠውን ከሀምሌ አንድ እስከ ነሀሴ 30 የተማሪ ምዝገባ የምዝገባ ጊዜ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አልቀበልም በማለት የራሱን የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት ከሀምሌ 1 እስከ 15 አድርጎ እንደነበር የነገሩን ፀሀፊው ለወረዳው ትምህርት ፅህፈት ቤት አመልክተው ወረዳው በወሰደው እርምጃ መሰረት የምዝገባው ጊዜ ወደ ነበረበት እንደተመለሰም ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትና ሬጉላቶሪ ማረጋገጫ ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ “መንግስት ከሚከተለው የነፃ ገበያ ፖሊሲ አኳያ በግል ትምህርት ቤቶች አሰራር ላይ ገብቶ ክፍያ ጨምሩም ሆነ ቀንሱ ማለት አይችልም። ወሳኞቹ ባለ ሀብቱና ወላጆች ናቸው። በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ነው መቀነስም ሆነ መጨመር የሚቻለው። በድርድር እንዲፈቱም ነው

የሚጠበቀው እንጂ እኛ እንደ ከተማ አስተዳደር ገብተን ዋጋ መወሰን አንችልም።” በማለት መልሰዋል።

በመመሪያው መሰረት በኛ በኩል ቀደም ብለን ለሁለቱም ወገኖች የጋራ መድረክ ፈጥረን እንዲወያዩ አድርገናል። ይህንን ያደረግነውም ካልተስማሙ ከወዲሁ ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ በማሰብ ነው የሚሉት ወይዘሮ ፍቅርተ የእሳቸው ቢሮ ኃላፊነት የትምህርት ጥራትን መከታተልና ደረጃውን እንዲጠብቅ ማድረግ ሲሆን፤ የክፍያ ጉዳይ የሁለቱ ወገኖች የድርድር ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ ሁለት ሺህ የግል ትምህርት ቤቶች ሲገኙ 958ቱ ጭማሪ ማድረጋቸውን ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ዘመን


► መረጃ ፎረም - JOIN US