በኤርትራ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን ለመጨረስ ሲቃረቡ ሳዋ ማሰልጠኛን በግዳጅ ይጎበኛሉ ተባለ

በኤርትራ የተደነገገዉ የግዳጅ ብሔራዊ ዉትድርና ወጣቱ ወደ አዉሮጳ ለመሰድድ ዋና ምክንያት ነዉ ሲል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት «HRW» ይፋ ባደረገዉ ዘገባ አመለከተ። HRW በዘገባዉ ኤርትራ ዉስጥ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን ለመጨረስ ሲቃረቡ መንግሥት ከመኖርያ ራቅ አድርጎ ያቋቋመዉን የሳዋን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ እንዲጎበኙ እንደሚያስገድድ በዘገባዉ አጋልጦአል።

የኤርትራ ወጣቶች በሳዋ ማሰልጠኛ ካምፕ በዉትድርና ፤ በመምህርነት፤ በግብርና ብሎም በረዳት ሕክምና ሞያ በመሳሰሉት ስልጠና ከተሰጣቸዉ በኋላ በመንግሥት ተቋም ሕይወታቸዉን ሙሉ እንዲያገለግሉ እንደሚደረግ ዘገባዉ አመልክቷል። የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ተቋም ፤ 3.2 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኤርትራ 500 ሺህ ሕዝብ ሃገሪቱን ጥሎ መሰደዱን ያስታወቀዉ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ከነዚህ ተሰዳጆች መካከል ከሦስት አንዱ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ሕጻን መሆኑን አሳዉቋል።

ወጣቶች ብሔራዊ ዉትድርና ካምፕ ላለመግባት ሲሉ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን ሆነ ብለዉ ለመድገም መገደዳቸዉንም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አጋልጧል። አንዳንዴ አፍሪቃዊትዋ ሰሜን ኮርያ በመባል የምትጠራዉ ኤርትራ በጎርጎረሳዉያኑ 2000 ዓም የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ ራስዋን ከተቀረዉ ዓለም አግልላ መቆየትዋ ይታወሳል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US