በሰኔ 15ቱ ጥቃት የሟች ፖሊሶች ቤተሰቦች ድጋፍ አልተደረገልንም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

ዶይቼ ቬለ DW – በሰኔ 15ቱ ጥቃት ባለቤቶቻቸው የሞቱባቸው የፀጥታ አካላት ባለቤቶች እርዳታ አላገኘንም አሉ። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የተሰው የፖሊስ አባላትን ያለልዩነት ለማገዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ዶይቼ ቬለ DW ካነጋገራቸው ሁለቱ እናቶች አንደኛዋ የባለቤታቸው የጡረታ መብት መከበሩን እንዲሁም የስድስት ወር ደሞዝ ማግኘታቸውን ቢገልፁም ከ4, ሺህ ብር በላይ የወር የቤት ክራይ እየከፈሉ ሦስት ሕጻናትን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ። ድርስ ነፍሰጡር መሆናቸውን የተናገሩት ሌላኛው በበኩላቸው የጡረታ መብታቸውን ተሯሩጠው ማስፈፀም እንዳልቻሉ፤ የስድስት ወር ደመወዝም እንዳላገኙ ገልጸዋል።

ወ/ሮ ፍሬሕይወት ጠና ባለቤቶቻቸውን በሞት ካጡ ሴቶች መካከል አንዷናት። ዕድሜዋ 22 ዓመት እንደሆነ የምትናገረው ፍሬሕይወት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በቅርቡ አጠናቅቃ ሥራ በመፈለግ ላይ ነበረች። የኑሮ አጋሯን ካገኘች በኋላ ኑሮዋን ከነፋስ መውጫ ወደ ባሕር ዳር አድረጋ ነበር። ባለቤቷ በሰኔ 15ቱ ጥቃት ከመሞቱ በፊት የመጀመሪያ ልጇን ለመገላገል ወደ ቤተሰቦቿ ነፋስ መውጫ መሄዷንም ትናገራለች። ሆኖም ሰኔ 15 ባለቤቷ በተፈጠረው ግጭት መሞቱን መስማቷን ሀዘን በተጫነው ስሜት ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግራለች። የመጀመሪያ ልጇን ለመውለድ ቀናት የቀሯት ወይዘሮ እስካሁን ከየትኛውም አካል ምንም እገዛና ድጋፍ እንዳልተደረገላትና በቅርቡ የሚወለደው ልጇ የወደፊት እጣፋንታም እንደሚሳስባት አመልክታለች። እርግዝናዋ ካሳደረባት ተፀዕኖ አንፃር የጡረታ መብቷን ተሯሩጣ ማስፈፀም እንዳልቻለች፣ እንዲሁም የኮሚሽኑ መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት የ6 ወር ደመወዝም እንዳልገባላት አስረድታለች።

ሌላዋ ያነጋገርናትና ባለቤቷን በግጭቱ ያጣችው ደግሞ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተወልደ ናት፡፡ ወ/ሮ ፍሬህይወት ተወልደ መዋዕለ ህፀናትን ያልተሸገሩ የሦስት ሕፃናት እናት ናት። 4, 500 ብር ኪራይ እየከፈለች እንደምትኖር የምትናገረው ወ/ሮ ፍሬሕይወት የቀበሌ ቤት ለመስጠት ቃል ከመግባቱ ውጭ ያደረገልኝ ነገር የለም ብላለች። የጡረታ መብቷን ማስጠበቋን፣ በፖሊስ ኮሚሽን መመሪያ መሰረት የስድስት ወር ደመወዝ መቀበሏንም ተናግራለች። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ በበኩላቸው የተሰው የፖሊስ አባላትን ያለልዩነት ለማገዝ ጥረት እተደረገ መሆኑን አመልክተው፣ ከጥረቶች መካከልም የሰራዊቱ አባላት ከደመወዛቸው 10 ከመቶ እንዲሰበሰብ ወስነዋል ብለዋል። እንደዚሁም የኮሚሽኑ መመሪያ በሚፈቅደው መሠሰረት ለእንዳንዱ ተጎጂ ቤተሰብ የስድስት ወር ደመወዝ ይሰጣል ነው ያሉት።


► መረጃ ፎረም - JOIN US