የአቦይ ፕሮፌሰር መስፍን መነሻና መድረሻ

ከቴዎድሮስ ሃይለማሪያም (ዶ/ር)

በቀደምለት አቦይ መስፍን ‹‹የአማራ ፋሽስቶች›› የምትል ነገር በፊስቡክ ለጥፈው ጥቂት ትኩረት መሳብ ችለው ነበር፡፡ ምናልባትም ሶስት ተከታታይ የስድብ መፃህፍት ስላወጡ ፣ ከተሳካላቸው አራተኛውን በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይዘው ለመምጣት ሳያስቡ እንደማይቀሩ እገምታለሁ፡፡ እስከዚያው መስፍን ባረጁበት ማናለብኝነት ‹‹ፋሽስት›› የሚለውን ፍረጃ የተጠቀሙት ‹‹እናትክን›› እንደሚለው የብልግና ስድብ በመሆኑ መልስ መስጠት አያስፈልገውም ነበር፡፡ ነገር ግን በርካታ ሰዎች ሰውየው ይህን ያህል የበገኑበትን ምክንያት ስለጠየቁኝ እንደሚከተለው ላስረዳ፡፡

1. የመስፍን መነሻ
(በውይይት መፅሄት ቁ.21 ላይ ‹‹አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻው የአማራ ህዝብ ጥያቄ›› በሚል ርዕስ ያቀረብኩት ፅሁፍ ነው፡፡ እሳቸውን የሚመለከተው በአጭሩ እነሆ)
‹‹የመስፍን መላምት ፤ ‹‹አማራ የለም !››
‹‹አማራ የለም!›› የለዘብተኛ ፖለቲካ ፍልስፍና ቃና ያለውና ብዙውን ጊዜ ራሳቸውንም ብሄረሰቡንም ከ‹‹አማራ›› ይልቅ ‹‹አማርኛ ተናጋሪ›› ብለው ከሚጠሩ ወገን የሚሰነዘር ነው፡፡

እንደምናስታውሰው ፕሮፌሰር መስፍንን ትዝብት ላይ የጣላቸው ወለምታ ነበር፡፡ ምናልባት በመጥፎ ወቅት የተሰነዘረ ቀና አስተያየት ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› ብለውታል፡፡ መስፍን ከዚያ ታሪካዊ ክርክር በኋላ ሃሳባቸውን ያሻሽሉት ወይስ በዚያው ይፅኑ አላውቅም፡፡ አንዳንዴ ግን የትችት አለንጋቸውን ወይ የአማራ ህዝብ ላይ ወይ የአማራ ልሂቅ ላይ መሰንዘር ስለሚቀናቸው ፣ መቼም የሌለ ህዝብ አይተቹም የሚል እምነት አለኝ፡፡››

2. የመስፍን መድረሻ
(በግዮን መፅሄት ቅፅ 1 ቁጥር 6 ላይ ‹‹የአማራ ምሁራንና ብአዴን ከጣውንትነት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ያቀረብኩት ፅሁፍ ነው፡፡ እሳቸው የቆነፀሉት እነሆ:-

‹‹የአማራ ብሄርተኝነት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ስጋት የማይሆንበት ተጨማሪ ምክንያት የብሄረሰቡ ትክለ ስብዕና ነው፡፡ አማራ የጥበብ መሃንዲስ ፣ ታሪክ ሰሪ ፣ ድንበር አስከባሪ ፣ አስተዋይ መሪ ነው፡፡ ለአከርካሪው ሲቃጡት አናት የሚያፈርስ የጀግኖች አውራ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቤተሰብነቱ አማራ የእግዜር የበኩር ልጅ ነው፡፡ በሃይማኖቱ ፣ በቁርጠኝነቱ ፣ በደግነቱና በትዕግስቱ ያሰበበት ደራሽ ነው፡፡››

ይሄኛው መስፍን ለመጀመሪያው ፅሁፍ መልስ የሰጡበት የተለመደው ስልታቸው ነው፡፡ ትሁት ለመምሰል በመጀመሪያ የፅሁፋቸውን ምንጭም የፀሃፊውንም ማንነትም ሳይጠቅሱ ‹‹የዚህ ፅሁፍ ቋንቋ ይጠና›› የሚል ማሳሰቢያ አስቀምጠዋል፡፡ እኔ በበኩሌ ያነበብኩት ‹‹ጠመንጃው በእጃችሁ›› እንደሚለው ታሪካዊ ሾርኒያቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንባቢያን ልብ እንዲሉት የምፈልገው መስፍን ‹‹ይጠናልኝ›› የሚሉት ከፅሁፌ ውስጥ ‹‹ቤተሰብነቱ›› የምትለዋን ውንጀላቸውን የምታፈርሰውን ቃል ሰርቀው ካስቀሩ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ የበለጠ ‹‹መሸጦነት›› ከየት ይገኛል?