10 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ የደረሰበት የምድር ባቡር ድርጅት በወንበዴዎች ዝርፊያ ተማረርኩ አለ

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ከወር በፊት ገጥሞት በነበረው መጠነኛ አደጋ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት መክሰሩንና በወንበዴዎች ዝርፊያና ስርቆት እየተቸገረ መሆኑን ገልጿል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል 167 ሺ 722 መንገደኞችንና 1ሺ248 የጭነት ባቡሮች ዕቃዎችን በማጓጓዝ 54 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም አስታውቋል፡፡

ከቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ይፋዊ የሚዲያ ጉብኝት ላይ ዋና ዳይሬክተሩ ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ከወር በፊት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱና የመስኖ ግድብ ፈንድቶ ጎርፍ ወደ ባቡር መስመሩ በመግባቱ፣ ሃዲዱን አንድ ኪሎ ሜትር የሚሆን ርቀት ጠልፎ ወስዷል፡ ፡ በዚህም መጠነኛ አደጋ ገጥሞት የነበር ሲሆን፣ በተፈጠረው አደጋም ሁለት የባቡር ሎኮሞቲቮችና አሥራ ዘጠኝ ፉርጎዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

የደረሰው ጉዳት በአጠቃላይ በገንዘብ ሲተመን አስር ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን፤ ድርጅቱ የመድኅን ዋስትና ያለው በመሆኑ የተጎዱትን ንብረቶች ለመጠገንና የደረሰውን ኪሳራ ለማካካስ ከኢንሹራስ ድርጅቶቹ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዓመት ከስድስት ወራት የሥራ ቆይታው ውስጥ የምድር ባቡሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት መሆኑንና ለአብዛኞቹ መፍትሔ እየሰጠ መምጣቱን ያስታወሱት ኢንጅነር ጥላሁን፣ በወንበዴዎች ዝርፊያና ስርቆት እየተቸገረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “ ድርጊቱ የሚፈጸመው በጨለማ በመሆኑ ወንበዴዎች የሚፈጽሙት ስርቆት ለመከላከል አስቸጋሪ ሆኖብናል” ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ የባቡር መንገድ የሚገነባው እያንዳንዳቸው ሃያ አምስት ሜትር ርዝመት ያላቸውን ሃዲዶች በመገጣጠም መሆኑን አመልክተው፤ “በአብዛኛው ስርቆቱ የሚፈጸመው እነዚህ ሃዲዶችን ለማያያዝ በሚያገለግለው ‹ፊሽ ብሌት› በሚባሉ ዋና የባቡር ሃዲድ መገጣጠሚያ ብሎኖችና በሌሎችም መለስተኛ ብሎኖች ላይ ነው” ብለዋል፡፡

ለአብነትም በቢሾፍቱና በእንዶዴ መካከል በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ የሚሆኑ ብሎኖች መሰረቃቸውንና ይህም እስከ አንድ መቶ ሺ ዶላር የሚገመት ዋጋ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ የሚፈጸመው በአብዛኛው ጭለማን ተገን አድርጎ በሌሊት በመሆኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ያም ሆኖ ግን ከአካባቢው ማህበረሰብና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር የወንጀለኞቹን መነሻና መድረሻ በመለየትና እጅ ከፍንጅ የሚያዙትን እንዲቀጡ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ምድር ባቡሩ ሥራ ከጀመረበት የፈረንጆቹ ጥር 2018 ጀምሮ የህዝብና የጭነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህም የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 167 ሺ 722 መንገኞችንና በ1ሺ 248 የጭነት ባቡሮች ዕቃዎችን በማጓጓዝ 54 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡

ምንጭ – አዲስ ዘመን


► መረጃ ፎረም - JOIN US