በምዕራብ ሐረርጌ በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት ነዋሪዎች ተገደሉ

DW : በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቦርደዴ ወረዳ ጉምቢ በተባለ ቦታ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የቦርደዴ ጤና ጣቢያ ባልደረባ ለዶይቼ ቬለ DW ተናገሩ።

የኦሮሚያ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ጥቃቱ መፈጸሙን በፌስቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መረጃ አረጋግጧል። የአፋር እና የኦሮሚያ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ በምትገኘው ጉምቢ በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱ ሰዎች መካከል አንዲት እንስት እንደሚገኙበት እና ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን የቦርደዴ ጤና ጣቢያ ባልደረባ የሆኑት ሲስተር ሃይማኖት ተስፋዬ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። «ሌሊት በዚያው በተኙበት ነው የገደሏቸው።

ሰባት ሰው ሞቷል። አሁን ሰባት እሬሳ አለ። እየተፈለጉም ያሉ አሉ፤ ማለት የጠፉም አሉ ተገድለው እንግዲህ እሬሳቸው ያልተገኘ ማለት ነው።ሲስተር ሃይማኖት ከሞቱት ሰባት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ሴቶች መቁሰላቸውን እና ወደ አሰቦት ሆስፒታል መላካቸውንም ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የገቡበት ያልታወቀ ሰዎች በመኖራቸው ፍለጋ እየተካሔደ ነው። ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር እና ድሬዳዋ የሚወስደው መንገድ ለረዥም ሰዓታት ተዘግቶ እንደነበር ተሰምቷል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US