DW : አንድ መቶ ሃያ አፍሪካውያን ስደተኞች የጫነ የስፔን የግብረ-ሰናይ ድርጅት መርከብ በአውሮፓ ወደቦች መቆም ተከልክሎ ባሕር ላይ ስድስተኛ ቀኑን አስቆጠረ። መርከቡን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ፕሮ አክቲቫ ኦፕን አርምስ የተባለ የስፔን የግብረ-ሰናይ ድርጅት አፍሪካውያኑን ስደተኞች ከባሕር የታደገው ባለፈው ሐሙስ እና አርብ መሆኑን አስታውቋል።
ድርጅቱ እንዳለው ስደተኞቹ በሊቢያ የገጠማቸውን መጎሳቆል የሚያሳዩ ምልክቶች በአካላቸው ላይ ይታያል። የጣሊያን የባሕር በር ጠባቂዎች በመርከቡ ላይ ከነበሩ ስደተኞች ባለፈው ቅዳሜ ሁለት ነፍሰ-ጡሮች እንዲወርዱ መፍቀዳቸውን የግብረ-ሰናይ ድርጅቱ አስታውቋል። የመርከቡ ካፒቴን ማርክ ሬይግ ለስደተኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት የጉዟቸው ማብቂያ መቼ እንደሚሆን በእርግጠኝነት የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
«ጉዟችን መቼ አልቆ ከመርከቡ እንደምንወርድ የማውቀው ነገር የለም። ምን አልባት ነገ፣ ከነገ ወዲያ አሊያም ከአምስት ቀናት በኋላ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጠንካራ መሆን አለብን። የገባንበትን በአሸናፊነት ለመወጣት ጠንካራ መሆን አለብን። ነገር ግን አውሮፓ እንደርሳለን»መርከቡ በአሁኑ ወቅት በጣልያኗ ላምፔዱሳ ደሴት እና በማልታ መካከል በሚገኝ ዓለም አቀፍ የውሐ አካል ላይ እየተንሳፈፈ ይገኛል። ማልታም ሆነች ጣልያን መርከቡ በወደባቸው እንዲቆም ፈቃደኛ አልሆኑም።
ባለፈው ሰኞ የጣሊያን ምክር ቤት ፈቃድ ሳይሰጣቸው በአገሪቱ ወደቦች የሚቆሙ መርከቦች ከአንድ ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚቀጣ ሕግ አፅድቋል።