በአዲስ አበባ በሌለበት 40 ዓመት የተፈረደበት ግለሰብ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ተኩስ መክፈቱ ተሰማ

DW :  በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተከሶ በሌለበት ወደ 40 ዓመት ገደማ የተፈረደበት ግለሰብ በሚከታተሉት ፖሊሶች ላይ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ተኩስ ከከፈተ በኋላ ጥይት ጨርሶ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተሰማ። የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት ከእስር ለማስለቀቅ ተደረገ የተባለው ሙከራ ሀሰት መሆኑ ተገልጿል።

ታምራት በቀለ ቶላ የተባለው ግለሰብ በወቅቱ ከፀጥታ ኃይሎች ለማምለጥ በከፈተው ተኩስ ሰበብ በስፍራው የትራፊክ እንቅስቃሴን ሲያስተናብሩ የነበሩ አንዲት የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል። ግለሰቡ በፖሊሶች ክትትል ውስጥ መሆኑን ሲረዳ ላዳ ታክሲ ተከራይቶ ከግብረ አበሮቹ ጋር ሲጓዝ ፖሊሶቹ እንዲቆም በማሰብ ላዳ ተሽከርካሪው ፊት ላይ ፒክ ተሽከርካሪያቸውን ሲያቆሙ ወንጀለኛው ታጥቆት የነበረውን ስታር ሽጉጥ በመጠቀም ተኩስ መክፈቱንና አሻፈረኝ በማለት ለማምለጥ መሞከሩን የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሃላፊ ኮማንደር ተክሉ ለታ በተለይም ለ ዶቼ ቬለ DW ተናግረዋል።

በዕለቱ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ የተከሰተውን ግርግር እስር ላይ የሚገኙትን የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሙሃመድ ዑመርን ለማስለቀቅ የተሞከረ ድርጊት ነው ተብሎ የተነገረው የተሳሳተ መረጃ መሆኑን የቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ኃላፊ ኮማንደር ተክሉ ለታ በተለይ ለዶይቼ ቬለ DW ገልጸዋል። ኮማንደር ተክሉ በስም የተጠቀሰው ተፈላጊው ወንጀለኛ ጥይቱን ከጨረሰ በኃላ አንድ መጋዝን ጣራ ላይ በመውጣት ሮጦ ለማምለጥ ቢሞክርም ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ለምርመራ ተልኮ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል። በዕለቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበራቸው እና በተለያዩ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ያሉት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙም ኮማንደር ተክሉ አክለው ተናግረዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US