የጅምላ እስር ፣ በባላደራው ላይ የሚደረገው ወከባ …ይቁም – መኢአድና ስድስት ድርጅቶች

መረጃ ቲቪን ሰብስክራይብ በማድረግ ወቅታዊ ዜናዎችን፣ ትንተናዎችን፣ የኪነጥበብ ፕሮግራሞችን እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ማግኘት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ (ኦነንፓ)፣ የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ (አሕነፓ) እና የአፋር ሕዝብ ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አሕፍዴፓ) በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ በመግለጫቸው  በሕወሃት ጊዜ ይታይ የነበረው የሰብአዎ መብት ረገጣ እየቆጠቆጠ መምጣቱና በፊት ወደነበረው ሁኔተ የመመለስ ዝንባሌ እንዳለ በመገልጽ መንግስት በአስቸኳይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለዜጎች መብት እንዲቆም ጠይቀዋል።

በመግለጫው ሰባት ነጥቦች የተቀመጡ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ በተለየም በጋዜጠኛና ሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንደር ነጋ የሚመራውን የባላደራውን ምክር ቤትን በስም በመጥቀስ ፣ ንቅናቄው በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የሚያራምደውን እንቅስቃሴ ያለምንም ችግር ማድረግ እንዳለበት በማስቀመጥ፣ ለባላደራው አጋርነታቸው ገልጸዋል።

የባላደራው ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን “ጦርነት ውስጥ ነው የምንገባው” ንግግር ተከትሎ በርካታ የኦህዴድ ባለስልጣናት ባላደራው ላይ ተመሳሳይ ዛቻ ማድረጋቸው፣ ባላደራው ስብሰባዎች እንዳያደረግ፣ ጋዜጣዊ መገጫዎችን እንዳይሰጥ መከልከሉና አባላቱም እየታሰሩበት መሆኑ ይታወቃል።

ድርጅቶቹ በመገጫቸው ያስቀመጧቸው  አሁን እየተወሰደ ያለው ዘርን መሰረት ያደረገ እስራት፣ ጅምላ ፍርጃ በአስቸኳይ ቆሞ ህግን መሰረት ያደረገ አሰራር እንዲዘረጋ፣ በመላ አገሪቱ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በአፋጣኝና ተገቢ በሆነ መልኩ ምላሽ መስጠት፣ በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ህይወታቸው ባለፈው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ጉዳይ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ፣የሰኔ 15ቱን ግድያ ተከትሎ ያለበቂ ማስረጃ በጅምላ በየቦታው የታሰሩ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የፓርቲ አመራሮች አባላት እና ንፁሀን ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣የሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ ህጉን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ሆኖ በዚያ ሳቢያ በንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያ፣ ዝርፊያና ወከባ የፈፀሙ ቡድኖች ወደ ህግ እንዲቀርቡ፣አዲስ አበባን በተመለከተ ባላደራው ይዞት የተነሳውን ሰላማዊ ጥያቄ ህግን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እንዲስተናገድ እና አዲስ አበባን በተመለከተ የነዋሪዎቿን እና የሁሉን ኢትዮጵያውያን ከተማ መሆኗን ፓርቲዎቹ  ጽኑ እምነት እንዳላቸው አሳውቀዋል።

የሰባቱ ድርቶች መግለጫ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል

————————-

በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከ7ቱ የተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

በአሁኑ ወቅት በመላ አገራችን ኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ የሰብአዊ እና የዲሞክራሲያዊ መብት ረጋጣዎች ከግዜ ወደ ጊዜ እያቆጠቆጡ መምጣታቸው ኢህአዴግ ትላንት ይዞት የነበረው ህገ-ወጥነት አካሄድ ያለቀቀው እና መቼም የማይለቀው መሆኑን ያረጋገጥን ሲሆን የመጣንበት ሂደትም ይህንን ያሳያል ፡፡

የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትን እና የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግድያን ተከትሎ እየተፈፀመ ያለው የጅምላ እስራት፣ ማሳደድ፣ ማሥፈራራት በአሥቸኳይ ቆሞ ህግና ሥነሥርዓትን የተከተለ አሰራር እንዲሰፍን እየጠየቅን የሟቾች ሁኔታ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ በማያሻማ መልኩ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለመላው የዓለም ሊገለፅ ይገባዋል፡፡ በመላ አገሪቱ እየታሰሩ ያሉት የፓርቲ አመራሮችና አባላት ሰበብ እየተፈለገ የተወሰደው የእስር እርምጃ ከዚህ ቀደም የአሸባሪነት ታርጋ በመለጠፍ ከተወሰደው ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ ይህ ድርጊት ቆሞ ንፁሀን ዜጎች ከእሥራት ሊፈቱ ይገባል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ ታስረው የሚገኙ የመንግስት ባለሥልጣናትና ንፁሀን ዜጎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ከእሥር እንዲለቀቁ እያሳሰብን በሌሎች ላይ የሚደረገውን ማዋከብ እንዲቆምና ዜጎች ተረጋግተው ሠላማዊ ኑሮአቸውን እንዲመሩ መደረግ ይኖርበታል ብለን በፅኑ እናምናለን፡፡ በአገራችን ደቡብ ክልል ከሚነሱ የክልል ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያ፣ ዝርፊያ ወከባ የሚፈፅሙ ቡድኖች ተጠያቂ እንዲሆኑና ለህግ ቀርበው የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንጠይቃለን፡፡ ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአፋጣኝና መብትንና ግዴታን መሰረት ባደረገ መልኩ ምላሽ መስጠቱ ጉዳት የሌለው ትርፋማ ውጤት ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

ይህንን ስንል የአገራችንና የሕዝባችንን አንድነት እያናጋ ያለው ዘርንና ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፌደራል መንግስት አወቃቀር መሆኑን እናምናለን፡፡ ይህን ስንታገለው የቆየ እንደመሆኑ መጠን ሌሎች ችግሮችም ይህንን ተከትሎ አገራችን እንዳታስተናግድ ብለን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የህገ-መንግስት የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በፅኑ እንገልፃለን፡፡
በሌላ መልኩ የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የሚነሱ እሰጥ-አገባዎች የተፈጠሩት የህግ-ጥሰቶች ታርመው ባላደራው የሚያደርጋቸውን ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች በተገቢው መንገድ የሚስተናግዱ ሆነው በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ የሚደረገውን ማዋከብ መቆም እንዳለበት እየገለፅን መንግስት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሳናጣራ አናስርም አስረንም ማስረጃ አንፈልግም” ባሉት መሰረት ማንኛውም ሰው በተናገረው ልክ የተለየ ሃሳብ ይዞ በመምጣቱ ሊታሰርም ሆነ ሌላ ጫና ሊደርስበት አይገባም፡፡ በዚህም መሰረት መንግስት የዜጎችን የሃሳብ ነፃነትን እንዲያከብር እንጠይቃለን፡፡

በትግራይ እና በአማራ ክልል የሚደረጉ የተንኳሽነት እሰጥ-አገባ ንትርክ በአስቸኳይ ቆሞ የሁለቱን ህዝብ ታሪካዊ ግንኙነትን መሰረት ባደረገ መንገድ የሚነሱ ጉዳዮችን መፍትሄ መሰጠት ይኖርባቸዋል ብለን በፅኑ እናምናለን፡፡ በመሆኑም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው እየጠየቅን፣ ጉዳያቸው በፓርቲዎች ም/ቤት ቀርቦ እንዲታይ እንጠይቃለን፡፡

1ኛ. አሁን እየተወሰደ ያለው ዘርን መሰረት ያደረገ እስራት፣ ጅምላ ፍርጃ በአስቸኳይ ቆሞ ህግን መሰረት ያደረገ አሰራር እንዲዘረጋ፣
2ኛ. በመላ አገሪቱ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በአፋጣኝና ተገቢ በሆነ መልኩ ምላሽ መስጠት፣
3ኛ. በሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ህይወታቸው ባለፈው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ጉዳይ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ፣
4ኛ. የሰኔ 15ቱን ግድያ ተከትሎ ያለበቂ ማስረጃ በጅምላ በየቦታው የታሰሩ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የፓርቲ አመራሮች አባላት እና ንፁሀን ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣
5ኛ. የሲዳማ ህዝብ የክልልነት ጥያቄ ህጉን መሠረት ባደረገ ሁኔታ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ሆኖ በዚያ ሳቢያ በንፁሀን ዜጎች ላይ ግድያ፣ ዝርፊያና ወከባ የፈፀሙ ቡድኖች ወደ ህግ እንዲቀርቡ፣
6ኛ. አዲስ አበባን በተመለከተ ባላደራው ይዞት የተነሳውን ሰላማዊ ጥያቄ ህግን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እንዲስተናገድ እንጠይቃለን፡፡
7ኛ. አዲስ አበባን በተመለከተ የነዋሪዎቿን እና የሁሉን ኢትዮጵያውያን ከተማ መሆኗን ፓርቲዎቻችን በፅኑ ያምናሉ፡፡

መግለጫውን የሰጡ የፓርቲዎች ዝርዝር፡-
1. የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት
(መኢአድ )
2. የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ
ኢሕአፓ
3. የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት
(ኢዴህ)
4. የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ
(ኢብአፓ)
5. የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ
(ኦነንፓ)
6. የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ
(አሕነፓ)
7. የአፋር ሕዝብ ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አሕፍዴፓ)