የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ያለው የክልል አደረጃጀት ቢቀጥል የሚለውን አማራጭ መርጧል የሚል ጥናት ይፋ ሆነ

(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ በደቡብ ክልል የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ምላሽ ለመስጠት ያስጠናው ጥናት ውጤት ዛሬ ይፋ ሆነ።

ላለፉት ሰባት ወራት በምሁራን የተካሄደው የደቡብ ክልል አዲስ አከላለልን የተመለከተው ጥናት ውጤትን በተመለከተ ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የደቡብ ክልል የብዝሃነት ምልክት አብሮ የመኖር አርአያ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች የክልል ምስረታ ጥያቄ በክልሉ በስፋት ቀርቧልም ብለዋል።

እንዲህ አይነቱ ጥያቄ በደቡብ ክልል ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን ሃሳብ አመንጪነት 20 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል።

የጥናት ብድኑ ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተውጣጡ ምሁራንን የያዘ ሲሆን፥ ምሁራኑ በአንትሮፖሎጂ፣ ታሪክ፣ የህዝብ አስተዳደር፣ ፓለቲካ ሳይንስ እና ፌዴራሊዝም ተመራማሪ እና ልሂቃን ናቸው።

በጥናቱ ከአንድ ዞን በስተቀር በሁሉም የደቡብ ክልል ዞኖች የተውጠጡ ከ17 ሺህ በላይ ሰዎች መረጃ ተስብስቧል።

ጥናቱ የ1987ቱን የደቡብ ክልል አደረጃጀት ሂደት፣ የክልሉ ህዝቦች በአከላሉ ያገኙት ትሩፋት እና የአዳዲስ ክልሎች ምስረታ ጥያቄ መንስኤዎች ተዳስሰዋል።

የ1987ቱን የደቡብ ክልል አወቃቀር በፌዴራል መንግስት ውሳኔ በዘፈቀደ ነው ወይስ የክልሉ ህዝብ ተሳትፏል በሚለው ጉዳይ ህዝብ የሰጠው ምላሽ የደቡብ ክልል በመንግስት ተጠፍጥፎ የተስራ አይደለም የሚል ሆኗል።

የክልሉ ምሁራን ያለ መንግስት ተፅእኖ ክልሉ በደቡብ ክልልነት እንዲመሰረት ተስማምተው ክልሉ መመስረቱን ተናግረዋል።

በጥናት ውጤቱ መስረት አብዛኛው የክልሉ ህዝብ አሁን ያለው የክልል አደረጃጀት ቢቀጥል የሚለውን አማራጭ መርጠዋል።

ክልሉ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቢከፈል የሚለውም በሁለተኛ ደረጃነት በጥናቱ ተሳታፊዎች ተመርጧል።

የክልል ምስረታ ጥያቄዎች ለጊዜው ቢቆይ እና በእርጋታ ቢታይ የሚለውም በጥናቱ በሶስተኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል።