ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት በእጩነት የቀረቡት የአቶ ተመስገን ጥሩነህ ሹመት ፀደቀ

አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ።

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀምሯል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት በእጩነት የቀረቡትን የአቶ ተመስገን ጥሩነህን ሹመት አፅድቋል።

አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር የአማራ ክልል ህዝቦች ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በአብሮነትና መተሳሰብ መንፈስና ለዘመናት ሲኖሩ የቆዩ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ ስንከተለው በነበረው የተዛባ የፖለቲካ አስተምህሮ ምክንያት ዛሬ ላይ አንድነታችንና ሰላማችን አደጋ ተደቅኖበታል ብለዋል።

ይህንን ለሁለት አስርት አመታት ሲሰበክ የነበረውን የተዛባ የፖለቲካ አስተምህሮ ለማስተካከል እና በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የሚሰራን ማንኛውንም የፖለቲካ ሴራ ለማስወገድ ከክልሉ ህዝብ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ በርካታ ወቅታዊ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ እነዚህን ፈተናዎች በብቃት ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም ያላቸው መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ለዚህም በክልሉ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ የፀጥታ ሃይሉን አቅም የማሳደግና የመገንባት ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ነው ያሉት አቶ ተመስገን፥ ክልሉን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት ምክንያት ሳይሆኑ በሕግ አግባብ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከዚህ ባለፈም በክልሉ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና አዳዲስ የቱሪስት ማስህቦችን ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ።

አቶ ተመስገን ጥሩነህ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒውተር ሳይንስ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋም የለውጥ አመራር ያገኙ ሲሆን፥ በተለያዩ የፌዴራልና የክልል መስሪያ ቤቶች በሃላፊነት አገልግለዋል።

በዚህ መሰረትም የአማራ ክልል የርዕሰ-መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር፣ የኢትዮቴሌኮም ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣በሃገር መከላከያ ሰራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ኤሌክትሮኒክስ መምሪያ፣ቴክኒካል መረጃ መምሪያ እንዲሁም በሚኒስትር ማእረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ሆነው ሰርተዋል።

Source – FBC