የክልሉ ሃብት የፈሰሰባትን ሐዋሳን የግል ለማድረግ የሚሞከር አደገኛ አዝማሚያ እየተመለከትን ነው ተባለ

«የክልሉ ሃብት የፈሰሰባትን ሐዋሳን የግል ለማድረግ የሚሞከር አዝማሚያም እየተመለከትን ነው ይህ አደገኛ ነው» –  አቶ መልካሙ ኦጎ

« ሕዝቡ በሰላም ጥያቄው እንዲመለስ ትዕግስት ሊኖረው ይገባል»  – የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፊት አውራሪ የነበሩት የአቶ ወልደ አማኑኤል ዱባለ ታናሽ ወንድም የሆኑት አቶ ማሞ ዱባለ 

« ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከተፈለገ ግን አንድም ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል በሌላም በኩል ክልል የመሆንን ነገር ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ መስፈርት ማስቀመጥ ተገቢ ነው» – በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ 

ዶይቼ ቬለ DW – ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን ክልል የመሆን ጥያቄ በሚመለከት ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የቀረበለት የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ አምስት ወራት እንደሚቀሩትና ለሥራውም ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመለከተ። የሀብት ክፍፍልና የሕጋዊነት ጉዳዮችን አስመልክቶ ለተነሳው ደግሞ በ9 ቀናት ውስጥ ምላሹን እንዲያሳውቅ ለክልሉ መግለፁን አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ዶይቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው ሰዎች ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲታይ ፣ ህዝቡም እንዲታገስ መክረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በደቡብ ክልል በሽግግር ወቅት የነበረው የክልሎች አወቃቀር ቢመለስ፤ አምስት የሚሆኑ ክልሎችም ዳግም ቢመለሱ እና እውቅና ቢያገኙ መልካም ነው ይላሉ። ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከተፈለገ ግን አንድም ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል በሌላም በኩል ክልል የመሆንን ነገር ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ መስፈርት ማስቀመጥ ተገቢ እንደሆነም መክረዋል።

ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ መልካሙ ኦጎ ደግሞ በተለይ የሐዋሳ ጉዳይ እና የሃብት ክፍፍሉ ነገር ያሰጋኛል፤ የሌላ ውዝግብ እና ትርምስ ምንጭም እንዳይሆን ያሳስበኛል ነው የሚሉት።
«የክልሉ ሃብት የፈሰሰባትን ሐዋሳን የግል ለማድረግ የሚሞከር አዝማሚያም እየተመለከትን ነው ይህ አደገኛ ነው» ሲሉም አሳስበዋል።

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፊት አውራሪ የነበሩት የአቶ ወልደ አማኑኤል ዱባለ ታናሽ ወንድም የሆኑት አቶ ማሞ ዱባለ ደግሞ የሲዳማ ጉዳይ ሆን ተብሎ ታርቆ የቆየ መሆኑን አውስተው አሁን በሕዝቡ ይሁንታ እንዲወሰን መፈቀዱን አድንቀው ሕዝቡም በሰላም ጥያቄው እንዲመለስ ትዕግስት ሊኖረው ይገባል ብለዋል። የሲዳማ ክልል መሆንም የተለየ ሀገሪቱን የሚያስወጣት ወጭ አይኖርም ብለዋል።