ኢሕአዴግ ከየት ወዴት? (ሙሉቀን ተስፋው)

ኢሕአዴግ ከየት ወዴት? (ሙሉቀን ተስፋው)

ባለፉት ዓመታት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ለውጥ መፍጠር ቢቻልም ሥልጣኑን የተረከባው አካል ግልፅ የሆነ ፍኖተ ካርታ ባለማዘጋጀቱ የጠገበው ሒዶ የራበውና ሁሉም የእኛ ነው በሚሉ አካላት እጅ ወደቀ፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካው የANC በተራዘመ ሰላማዊ ትግል የመጣው የኢትዮጵያ ለውጥ በአግባቡ ኃላፊነት ከሚሰማቸው አካላት እጅ አለመውደቁ ለአገራችንና ለሕዝባችን ከመና ይልቅ ርግመትን አስከትሎ መምጣቱ ግልጽ እየሆነ ነው፡፡ የዶር ዐቢይ መንግሥት አንድም ሆን ብሎ፣ አሊም ካለማወቅና ከልምድ ማነስ በዘፈቀ እየሔደባቸው ያሉ መንገዶች አይደለም ለኢትዮጵያ ለኦሮሞ ሕዝብም የማይጠቅሙ ናቸው፡፡

በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ አቢዮት (Revolution)፣ ተሀድሶ (Renaissance) ወይስ ጥገናዊ ለውጥ (Reform) ነው? በሚለው ላይ ስምምነት የለም፡፡ ጠሚው በተለያዩ ጊዜያት የሚያደርጓቸው ርእስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ንግግሮችን ተስፋ የሚያደርገው ጎጋው ሕዝብ ቀናት አልፈው ወራት እየተተኩ በመጡ ቁጥር ምንም ጠብ የሚል ነገር አለመኖሩ ሕዝቡ የሰነቀው ተስፋ በአንዴ በንኖ የጠፋ ይመስላል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደጋፊ የነበሩ ተቃዋሚ ሲሆኑ፤ የድጋፍ ሰልፎች ወደተቃውሞ ሲቀየሩ፤ ሌላው ቀርቶ ውጭ የሚኖሩ ሀበሾች ሰልፍ እንዳይወጡ የሚያደርግ የአንድ ዓመት የዕፎታ ዘመን እንኳ ማምጣት አልተቻለም፡፡

የኢሕዴግ ጉዳይ!

ከ2008 ዓም በኋላ ኢሕአዴግ እንደፓርቲ ነበር ማለት የማይቻል ቢሆንም በቅርቡ በሚደረገው የፓርቲው ስብሰባ ይፋዊ ፍች እንደሚደረግ ከወዲሁ መገመት ይቻላል፡፡ ኢሕአዴግ የፈረሰው በፓርቲው ውስጥ የነበረው በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መረጃዎችን አፍኖ መያዝ ካቆመ በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ላይ ያሉት ከአራቱም እህት ፓርቲዎች ፈጽመው አይናበቡም፤ የሚያወጧቸው መግለጫዎች እንኳንስ በአንድ ፓርቲ ሥር ያሉ ሊያስመስላቸው በሕጋዊ ተቃዋሚ ስም እንኳ መንቀሳቀስ የማያስችል ነው፡፡ ከመዘላለፍ እስከ ጦርነት የደረሰ ግጭት በፓርቲዎቹ መካከል ተፈጥሯል፡፡ ትናንት ሕወሓት ያወጣው መግለጫ ከአዴፓ ጋር (በርግጥ ከአማራ ሕዝብ ጋር ለማለት ነው) አብሬ መቀጠል አልፈልግም በሚል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በመጎሻሸም የከረመው የፓርቲዎቹ ግንኙነት ከዚህ በኋላ በይፋ የሚያከትምበት ጊዜ ቢበዛ አንድ ወይም ሁለት ወር ብቻ ናቸው፡፡

የሕወሓት ጉዳይ!

ሕወሓትን እንደ ፓርቲ መጀመሪያ የገደለው የ1992ቱ ሕንፍሽፍሽ ነው፤ ከዚያ በመቀጠል መለስ በዙሪያው ከእኔ ይሻላሉ ያላቸውን ሰዎች ገደላቸው፡፡ በመጨረሻም ሰውየው ሲሞት ፓርቲውም በሕይወት አለ ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ እስከ 2008ትም የቆየው ቀደም ሲል በገነባው የአሰፈሪነት ስም ብቻ ነው፡፡
ለሕወሓት ሌላው ፈተና ደግሞ ተረካቢ አመራር አለመፍጠሩ ነው፡፡ ከጫካ የመጡት አገራዊ ሥልጣኑን ሲቆጣጠሩ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው የተሠማሩት በኮንትሮባንድ ንግድ ብቻ ነበር፡፡ በዚህም ይመስላል እስካሁን ድረስ አዲስ ሰው ወደፊት ሲመጣ የማይታየው፡፡ በኮንትሮባንድና በዘረፋ የነበሩ ልጆችን ወደ ሥልጣን ያመጡ ዕለት ደግሞ የሚፈጠረውን መገመት አይከብድም፡፡
የሕወሓት ጥንካሬና ድክመቶች!
ሕወሓት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሰበብ የተሠበሰበ ዘመናዊ የጦር መሣሪያና በኮንትሮባንድና ዘረፋ የተገኘ ተዝቆ የማያልቅ ገንዘብ አላቸው፡፡ በተጨማሪም ብዙ የትግራይ ወጣቶችን በጭፍን ብሔርተኝነት ሁሉም ሰው ይጠላናል እና በጦርነት እንዘጋጅ በሚል ሥነ ልቦና ለማጥመቅ ሞክረዋል፡፡ በተረፈ ግን ሕወሓቶች የጠነከረ የመሰላቸውን አብረን ነን የደከመ የሚመስላቸውን ደግሞ ከእናንተ ጋር ኅብረት የለንም የሚል የዋዥቅ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ትናንት ያወጡት መግለጫ ለምሳሌ ከእነ አምባቸው መሞት ጋር ተያይዞ አዴፓ ተዳክሟል በሚል እሳቤ ነው፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛዎቹ የሕወሓት አመራሮች የአደዋ ሰዎች ብቻ መሆናቸው የተንቤንና ሌሎች አካባቢ የትግራይ ተወላጆችን ትግል ለድርጅቱ ፈታኝ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

የኦዲፒ ጉዳይ!

አሁን ያለው ኦዲፒ የኦሕዴድ፣ የኦፌኮና የኦነግ ጥምር ነው ማለት ይቻላል፡፡ በደርጅቱ ውስጥ ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነትም በሰፊው ይንፀባረቅበታል፡፡ ለኦሮሞ ሕዝብ ቆመናል የሚሉት ከደርዘን በላይ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም የላቸውም፤ አሁን አብዛኛዎቹ በኦዲፒ ውስጥ በመካተታቸው በውጭ የነበረው ልዩነት በፓርቲው ውስጥ እየሠፋ ሒዷል፡፡ በአዴፓ ትክሻ ላይ ሆነው ያገኙትን ሥልጣን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው እንኳ ሁሉም እኩል በሆነ ደረጃ አያውቁም፡፡ ኦዲፒዎች ሦስት የሚታወቁባቸው ድክመቶች አሏቸው፡፡ አንደኛው ከኦዲፒ ሰዎች ጋር የተመከረ ሚስጢር ሪከርድ ከተሠበረ የመጨረሻ እድሜው 24 ሰዐት አይሞላም፡፡ በዚህም ምክንያት እነ ለማና ዐቢይ ብዙ ፈተና ገጥሟቸዋል፤ አዴፓዎችን ብዙ ዋጋ አስከፍለዋቸዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኦዲፒ ሰዎች ከበድ ያለ ፈተና አይችሉም፡፡ በጭንቅ ጊዜ ጥለው ዘወር የማለት ባሕሪ አላቸው፡፡ ለዚህም የኦዲፒ ሰዎች ይዞ ጦርነት ሊገጥም የሚችል እንኳንስ ከሌላ ፓርቲ እርስ በእርሳቸውም አይሆንላቸውም፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በመንገድ ያዩትን ሁሉ የእኛ ነው የማለት አባዜ ነው፡፡ ይህችኛዋ ከሕወሓት የወረሷት ጂኒ ሳትሆን አትቀርም፡፡

ኦዲፒዎች በጥንካሬ የሚያዝላቸው በርካታ የተማረ የሰው ኃይል አላቸው፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች በተለይ በውጭ የሚኖሩት በብዛት ተምረዋል፤ መማራቸው ብቻም ሳይሆን ሁሉም ትምህርታቸውን የሚያይዙት ከሕዝባቸው ጋር ነው፡፡ ይህ በፓርቲው የአማራር ክፍተት እንዳይፈጠር ሊያግዘው ይችላል፡፡ ሆኖም ሁሉም የተማሩ የኦሮሞ ምሁራን ተመሳሳይ አስተሳሰብ አላቸው ማለት አይቻልም፡፡

የአዴፓ ጉዳይ!

አዴፓ ውስጥ የሚታየው ትልቅ ድክመት ቀደም ሲል ከሕወሓት ጋር በማበር ሕዝብ ሲበድሉ የነበሩ ሁሉ ወደፊት በመምጣት የቀደመውን በደል ለመካስ በሚል ወይም በሌላ በስብእና ግንባታ ላይ ብዙ ጊዜያቸውን ማጥፋታቸው ነው፡፡ የአዴፓ አመራሮችን እስካሁን ባለው ጊዜ አክቲቪስት እንደፈለገ የሚያደርጋቸው ነው የሚመስለው፡፡ ይህ አካሔድም ፓርቲውን ብዙ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡

የፓርቲው አመራሮች ከአማራው ሕዝብ በላይ ለአገር ከመጠን በላይ የሚጨነቁ መሆኑም እንደ ድክመትም እንደጥንካሬም የሚያዝ ነው፡፡ ደመቀ ሥልጣኑን ለዐቢይ የሰጠበት አካሔድ ብንመለከተው ኢትዮጵያን አስቦ ካልሆነ ሌላ ትርጉም አይሠጠውም፡፡ ሌላው ደግሞ አዴፓዎች በኦዲፒዎች ላይ ከፍተኛ እምነት መጣላቸው እንደ ድክመት ቆይቶም ቢሆን የገባቸው ይመስለኛል፡፡ አዴፓዎች የተማሩ ሰዎችን የማቅረብ ዝንባሌያቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ አዴፓ ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶቹን ካስተካከለ የተሻለ ድጋፍ የማግኘት እድልም አለው፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US