እንግሊዝ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን በኢትዮጵያ ለመደገፍ እቅድ አወጣች

ብሪታኒያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የ12 ሚሊዮን ፓውንድ ዕቅድ ይፋ አደረገች። ዕቅዱ ይፋ የሆነው የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያዘጋጀው እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን መጠበቅ አስፈላጊነት ላይ የሚመክር ውይይት ላይ ነው።

የብሪታንያው ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት ኃላፊ ሐርየት ባልድዊን እንዳሉት ገንዘቡ የመገናኛ ብዙኃንን ለማጠናከር የታቀደ ነው። ሐርየት ባልድዊን «በዛሬው ዕለት የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ለመጠበቅ እና በማደግ ላይ አገሮች የሚገኙ መገናኛ ብዙኃንን ለማጠናከር የ12 ሚሊዮን ፓውንድ አዲስ እቅድ ይፋ አድርገናል። ዕቅዱ በመጀመሪያ ትኩረቱን በባንግላዴሽ፣ ሴራሊዮን እና ኢትዮጵያ ላይ በማድረግ ይጀምራል።

ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ወትዋቾች፣ የሕግ ተቋማት እና የሲቪል ማኅበራት ሐሳብን የመግለፅን እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን በመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት እና በሰሜን አፍሪካ እንዲደግፉ የ3 ሚሊዮን ፓውንድ መርሐ-ግብር ይፋ ሳደርግ ደስታ ይሰማኛል።» ብለዋል። በውይይቱ የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር መሐመድ ኢሴ አዋድ፤ የካናዳዋ አቻቸው ክርቲያ ፍሪላንድ እና የብሪታኒው ዤሮሚ ኸንት ተገኝተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ባለፉት ዓመታት ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አላቸው በሚባሉ ሃገራት ጭምር ጋዜጠኞች የሕዝብ ጠላት እየተባሉ መፈረጃቸው ሥራቸውን ፈታኝ እንዳደረገው ተናግረዋል። ከአምባገነን መንግሥታት እና አፋኝ ሕግጋቶቻቸው ያልተላቀቀችው አፍሪካ ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በእጅጉ እንደሚያስፈልጋት በዚሁ ውይይት ላይ ተገልጿል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US