ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ሊያደርጉ ነው

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንደሚያደርጉ በአዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ አስታወቀ።ኤምባሲው ዛሬ ባስተላለፈው መረጃ መሠረት ወታደራዊ ልምምዱ የሚካሄደው ከሐምሌ 8 እስከ እስከ ሐምሌ 24፣2011 ዓም ድረስ ነው። DW

 (ኤፍ ቢ ሲ)

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ወታደራዊ ልምምድ ሊያደርጉ ነው።

ወታደራዊ ልምምዱ የአሜሪካ መከላከያ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ጋር በጥምረት የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

ልምምዱ በሶማሊያ በተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አባላትን አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ወደ 1 ሺህ 100 የሚጠጉ ወታደራዊና የመንግስት ሃላፊዎች ይሳተፉበታል።

ልምምዱ የመከላከያ አባላትን ዝግጁነትና አቅም በማሳደግ ሰላምን ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉና በቀጠናው ሰላምን ለማስፈን እንደሚያግዝም ታምኖበታል።

የፊታችን ሰኞ የሚጀመረው የ2019 ወታደራዊ ልምምድ ለ17 ቀናት እንደሚቆይ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በወታደራዊ ልምምዱ ላይ ከብራዚል፣ ብሩንዲ፣ ካናዳ፣ ጂቡቲ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኬንያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም የተውጣጡ ወታደሮች ይሳተፋሉ።

ከዚህ ባለፈም እንደ አፍሪካ ህብረትና እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት፣ የአሜሪካ የሰላም ተቋምና ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር የተውጣጡ ባለሙያዎችም ይሳተፋሉ ነው የተባለው።

በተያተያያዘም ኢትዮጵያና አሜሪካ በህክምና ዝግጁነት ላይ ያተኮረ ልምምድ እያደረጉ ነው።

ይህ ልምምድ ወታደራዊና መደበኛ የህክምና አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን፥ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የሚሰጠውን የህክምና ክትትል አቅም ለማሳደግ ያስችላል ነው የተባለው።

በመንግስታቱ ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ከሁለት አመት በፊት ከአሜሪካ ጋር መሰል ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ይታወሳል። FBC