የታገዱት ሞተረኞች እሮሮ እያሰሙ ነው

BBC Amharic : አሸናፊ አህመድና ግርማይ ሞተር በመንዳት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማሻሻል ይታትራሉ። አሸናፊ እንደሚለው ባለፉት አስር ዓመታት በሞተሩ በእያንዳንዱ የከተማ ጥግ እየተንቀሳቀሰ ሰዎች ያዘዙትን ያመላልስ ነበር።

“ገንዘብም ሆነ እቃ አድርስ ያሉኝን በታማኝነት አደርስ ነበር” ያለው አሸናፊ የሁለት ልጆች አባት ነው።

አሸናፊም ይሁን ግርማይ ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ የተመሰረተው ሞተር መንዳት ላይ ነበር። አሁን ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ፈቃድ የሌለው ሞተር ከተማ ውስጥ ማሽከርከር ስለከለከለ፤ ሥራ አቁመው ቀን የሚያመጣውን ይጠብቃሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማው ሰላም ስጋት ናቸው ያላቸውን ሞተር ብስክሌቶች ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ እንዳይንቀሳቀሱ ያገደው ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ. ም. ነበር።

በ15 ቀን ውስጥ አስፈላጊውን ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮች በትራንስፖርት ቢሮ እንዲፈፅሙና ሕጋዊ እንዲሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አስታውቆ ነበር።

እነ አሸናፊን የከተማ አስተዳደሩ ተደራጅታችሁ ሥሩ ብሏል ምን እያሰባችሁ ነው? ተብለው ሲጠየቁ አማራጮችን ለመፈለግ ጊዜው አጭር መሆኑን ግርማይ ይናገራል።

የእለት ጉሮሯቸውን ከሚደፍኑበትን ሥራ ማፈናቀል ተገቢ አለመሆኑን በመቃወም ሞተር አሽከርካሪዎች ተሰብስበው ሰልፍ ማድረጋቸውንም ያስታውሳል።

ሰልፉን ሰኔ 26 ቀን 2011 ዓ. ም. ቢያደርጉም ምላሽ የሚሰጣቸው አካል ባለማግኘታቸው እንዳዘነ የሚናገረው ግርማይ፤ “ነገሩ ተስፋ ያለው አይመስልም” ይላል። አሸናፊም ጉዳዩን ወደሚመለከተው አካል ለመውሰድ ፍላጎት የለውም።

አሸናፊ፤ ሞተር ከማሽከርከር ውጪ ሥራ ለመቀየር ባያስብም፤ “ባሉት ስራ አጦች ላይ ሌላ ሥራ አጥ ሆኜ ተደምሬያለሁ” ይላል በቁጭት።

ሞተር በማሽከርከር በሚያገኙት ገቢ ቤት ተከራይተው ሦስትና አራት ልጅ የሚያሳድጉ፣ ወላጆቻቸውን የሚጦሩም አሉ የሚለው አሸናፊ፤ በእርግጥ አዲስ አበባ ውስጥ ወንጀል ስለተበራከተ መንግሥት ወንጀልን ለመከላከል እርምጃ ቢወስድም በርካቶችን ሥራ አጥ ማድረግ ደግሞ ተገቢ አይደለም ይላል።

በከተማዋ ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወንጀል ለመፈጸም ቢውሉም፤ ሞተር ላይ ብቻ እርምጃ መወሰዱ አስገርሞታል።

አሸናፊ፤ ደንቡ ሰኔ 30 ይተገበራል ቢባልም፤ ከሰኔ 15 ጀምሮ ሥራ እንዳስቆማቸው ይጠቅሳል። ግርማይ በበኩሉ ከሰኔ 28 ጀምሮ ሥራ እንዳስቆሟቸው ይጠቅሳል።

የ”ዘ ሞል ዴሊቨሪ” አገልግሎት ባለቤት አምባዬ ሚካኤል ተስፋዬም በመንግሥት እርምጃ ሥራቸው መጎዳቱን ይናገራል። “ሞተሮቻችን ቆመዋል” የሚለው አምባዬ፤ ሥራ ሙሉ በሙሉ ማቆማቸውን ይገልጻል።

የጥርስ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሰብለ ማሞ ድርጅታቸው በቤተ ሙከራ ውስጥ የሚያመርታቸውንና ለተለያዩ የጥርስ ክሊኒኮች የሚያቀርቧቸውን ትዕዛዞች በሞተር ያመላልሱ እንደነበር ይናገራሉ።

አሁን ግን ማቅረብ ባለመቻላቸው ደንበኞቻቸው እየተማረሩ መሆኑን ይገልጻሉ።

አምባዬ፤ ደንቡ ይፋ እንደተደረገ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችን ለማነጋገር መሞከራቸውን አስታውሶ፤ ደንቡን ያወጡትን አካላት ቢያነጋግሩም ምዝገባ የጀመሩት ባለፈው ሳምንት መሆኑን ይጠቅሳል።

የከተማ አስተዳደሩ ያቀረበውን መስፈርት ሙሉ በሙሉ ማሟላታቸውን አምባዬ ገልጾ “ሞተሩ ላይ ጂፒኤስ ማስገጠም፣ ሞተረኛውን የደንብ ልብስ ማልበስ የሚሉትን አሟልተን ብናቀርብም በምንፈልገው ፍጥነት ጉዳያችን እየተስተናገደ አይደለም” ይላል።

ማንን ማነጋገር እንዳለባቸው፣ ወይም የሚመለከተው ኃላፊ ማን እንደሆነ ግልፅ ያለ ነገር እንደሌለ የሚናገረው አምባዬ፤ በዚህም የተነሳ የተለያዩ ቢሮዎች ለመሄድና ደጅ ለመጥናት መገደዳቸውን ያክላል።

የዘ ሞል ዴሊቨሪ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተመስገን ገብረሕይወት፤ በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በርካታ አማራጮችን መኖር አለባቸው ይላሉ።

“በአሁኑ ሰአት ሞተር ብስክሌቶች ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ርካሽ አገልግሎት እየሰጡ ነው” በማለትም ስለ አገልግሎቱ ሀሳባቸውን አካፍለውናል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፤ በከተማዋ ሞተር በመጠቀም በተደራጀ መንገድ ቅሚያ፣ ስርቆትና አልፎ አልፎ ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ሰሌዳቸው የአዲስ አበባ ያልሆኑ ሞተር ብስክሌቶች ዋነኛ የችግሩ ምንጭ መሆናቸውን በማመልከት ነው የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ከሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ሞተሮች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን ያስታወቁት።


► መረጃ ፎረም - JOIN US