“የመከላከያው በአደባባይ ሚዲዎችን እከሳለሁ ማለት አስፈሪ ነው” ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ

BBC Amharic : በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል የቀድሞ ዲን እና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካው ኒው ሜክሲኮ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት ዶ/ር አብዲሳ ዘርዓይ ከጥቂት ወራት በፊት ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ለውጡን ተከትሎ የመጣውን የሚዲያ ነፃነት ሚዲያው በአግባቡ ካልተጠቀመበት መንግሥት ዳግም ሚዲያውን ወደ መጫን ሊሄድ ይችላል ብለው ነበር።

በአገር ውስጥ በተለይም በውጭ ሃገር በአክቲቪዝምና በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ሚዲያዎች አካሄዳቸውን አስተካክለው ነው ወደ ጨዋታው ሜዳ መግባት ያለባቸው ብለው ነበር። አሁን ደግሞ በቅርቡ ሚዲያው ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮችን በማስመልከት የተወሰኑ ጥያቄዎችን አንስተንላቸዋል።

ጋዜጠኞች እየታሰሩ ነው፤ አንዳንድ ፕሮግራሞችም እየታጠፉ ነው። ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የመከላከያ የተቋሙን ስም አጥፍተዋል፤ ሕዝብ ተቋሙን እንዲጠራጠር የሚያደርጉ ሐሰተኛ መረጃዎችን አሰራጭተዋል ያላቸውን ሚዲያዎች እከሳለሁ፤ ለመክሰስም ዝግጅቴን ጨርሻለሁ የሚል መግለጫ ሰጥቷል።

እነዚህ እስሮችና እንደ መከላከያ አይነት ትልቅ የመንግሥት ተቋም ምንም እንኳን ሚዲያዎቹን በስም ባይጠቅስም የምከሳቸው ሚዲያዎች አሉ ማለቱን እንዴት ነው የሚያዩት? ከዚህ ቀደምም ተመልሶ ወደኋላ የመሄድ ነገር ሊያመጣ ይችላል ብለውን ነበር።

ዶ/ር አብዲሳ፡ ሚዲያው የተሰጠውን ነፃነት በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ መንግሥት ዞሮ እንዳሁኑ ወዳለ ነገር ሊመጣ ይችላል የሚል ነገር ነበረኝ። በተለይም ደግሞ ህብረተሰቡ ሚዲያው ከመስመር የመውጣቱን ነገር እያየ ሲሄድ የመጀመሪያ የሚመጣው ምንድን ነው፤ ይህንን አድርግ [ኮንትሮል አድርግ] የሚል ነገር ስለሆነ መንግሥት ከዚያ በኋላ ለሚወስደው ነገር በሙሉ ትክክል እንደሆነ ህብረተሰቡ እንዲያይ የሚያደርግ ነገር ይሆናል።

ተገቢ ባይሆንም እንዲሁም ዞሮ ዞሮ የሐሳብ ነፃነትን እየገደበ የሚሄድና ነፃነት እያጨለመ የሚሄድ ነገር ቢሆንም በነፃነቱ ጊዜ የነበረው የሚዲያው ያልተገባ አካሄድ በማህበረሰቡ ዘንድ በአሉታዊ መልክ ስለሚታይ መንግሥት የሚወስደውን ከባድ እርምጃ ሁሉ እንደ ትክክለኛ ነገር የማየት አዝማሚያ ሊኖረው ይችላል። ከዚህ ቀደም የሚዲያ ነፃነቱን በአግባቡና ሙያዊ መርህን በተከተለ መንገድ ኃላፊነትን ታሳቢ አድርጎ መጠቀም አለበት ያልኩትም ነገር ይህ ነው።

አሁን አገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ የፖለቲካ ሁኔታዎች ሥርዓቱ ራሱ የተጨነቀ፤ የደነገጠበት[ነርቨስ] ሰዓት ነው። የትኛውም ዓለም ላይ የመንግሥታት የመጀመሪያው ተግባር [ኢንስቲንክታቸው] የራሳቸውን ደህንነት የማረጋገጥ ነው። ከዚያ በኋላ ነው ሌላው ነገር የሚመጣው። (ስለዚህ የራሱን ደህንንት ማረጋገጥ የየትኛውም መንግሥት የመጀመሪያ እርምጃ ነው።)

በአማራ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ የተከሰተውንና መንግሥት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው የሚለውን ነገር እንዲሁ ካመንን መንግሥት ምን ያህል ውጥረት ውስጥ እንደገባ የሚያመለክት ነው። (ስለዚህ የመጀመሪያው ኢንስቲንክት የራሱን ሰርቫይቫል ኢንሹር የማርደግ ጉዳይ ነው)። ይሄን ለማድረግ ደግሞ የትኛውንም አይነት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ የሚልበት አይደለም የሚሆነው። ስለዚህ አሁን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በጣም አሳሳቢ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ይታወቃሉ በገንዘብም በሙያዊ አቅም የዳበሩ አይደሉም። እንደ መከላከያ አይነት ትልቅ የመንግሥት የፀጥታ ተቋም ሚዲያዎችን እከሳለሁ ማለቱ ምን ያህል ሚዲያዎችን ሊያስፈራና ተፅኖ ሊያሳድር ይችላል ብለው ይገምታሉ?

ዶ/ር አብዲሳ፡ በጣም አስጊ ነገር ነው። ‘ሚሊተሪ’ [ወታደራዊ ኃይል] በአፍሪካ ውስጥ ሁሉም ነገረ ነው። በአብዛኛው የአፍሪካ አህጉር የወታደሩ ኃይል ታሪክ ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነገር ነው። ስለዚህ በአሁን ሰዓት በወታደሩ በኩል መጥቶ በዚህ መንገድ በአደባባይ ላይ ይህንን ነገር ወደ ተግባር ባያመጣውም እንኳን አስፈሪ ነገር ነው።

ሚዲያ ላይ የሚሠሩ ሰዎች በፍርሀት ራሳቸውን በጣም ሴንሰር እንዲያደርጉ፣ ነገ ምን ይከሰታል? ብለው የመደናገጥ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግም ጭምር ነው የሚሆነው። ሚዲያ ላይ ወጥቶ አስተያየት ለመስጠት የሚጋበዙ ሰዎችም ሁሉ እንደ ድሮው በፈቃደኝነት አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ የሚያደርግበት እድልም ሰፊ ነው።

ስለዚህ በተለይ አሁን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በሚል ስለሆነ የተቀመጠው [ዲፋይን] የተደረገው፤ መንግሥት ከዚህ ጋር ይገናኛል ወይም ለእሱ ድጋፍ ያደርጋል ያለውን ሁሉ የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ እንደ ጠላት የመወሰድ እድሉ ሰፊ ነው። መንግሥት በዚህ ሰዓት የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ ማንኛውንም ርቀት መሄድ የሚችልበት እድም ሰፊ ነው። በእኔ ፀሎት መከላከያ ይህንን ዛቻ ወደ ተግባር አይቀይረውም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አለበለዚያ በጣም ትልቅ የሆነ ችግር ነው ይዞ የሚመጣው።

መንግሥት ታዲያ ምንድነው ማድረግ ያለበት?

ዶ/ር አብዲሳ፡አግባብ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ መሄዱ ነው አስፈላጊ የሚሆነው። ለዚህም ነው ሚዲያ እንዴት ነው የሕግ አግባቦችን የሚከታተለው? እንዴት ነው የሚዳኘው? የሚሉትን ነገሮች መጀመሪያውኑ እየሠሩ የማስቀመጥ ነገር አስፈላጊ የሚሆነው።

ጋዜጠኞችን ጨምሮ ብዙዎችን ለእስርና ለስደት ያበቃው የፀረ ሽብር አዋጁ አሁን የታሰሩ ሰዎች ላይ እንደተጠቀሰ እየሰማን ነው?

ዶ/ር አብዲሳ፡አዎ አሁን ሰዎች እየተጠየቁ ያለው በቀድሞው የፀረ ሽብር ሕግ ነው። ሕጉ በመሻሻል ላይ እንዳለ ይታወቃል። መንግሥት በፍርሀት ውስጥ እየገባ የሚሄድ ከሆነ፤ አሁን የደቡብ ክልል ውስጥ ያለው የክልልነት ጥያቄ ሐምሌ 11 ይምጣና እንግዲህ እንተያያለን የሚሉት ነገሮች ሁሉም ምን አስከትለው እንደሚመጡ የሚታወቅ ነገር የለም።

የቀድሞ መንግሥት አሸባሪ ነው ብለው ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው በፓርላማ የተናገሩበት ሕግ እየተጠቀሰ አሁን ሌሎች እየታሰሩበት ነው። ነገሮች በዚህ አለመረጋጋት ከቀጠሉ አዲሱ ማሻሻያ እንደውም ወደ ተግባርም ላይመጣ የሚችልበት እድል አለ።

ምክንያቱም ይሄኛው ብዙ ነገሮችን ለማሰርና እንደተፈለገ ለማድረግ ብዙ ቀዳዳዎችን የሚሰጥ ስለሆነ ይሄንን አሻሽሎ የማምጣት የመንግሥትን ተነሳሽነት ሊያዳፍን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ይህ ደግሞ ሚዲያው ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ስለሆነ በአንክሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ሚዲያውን ራሳችሁ ባደረጋችሁት ይኽው ደረሰባችሁ ብለን የምናዜመው ነገር አይደለም።

ሚዲያው መንገድ ሲስት መስመሩን ተከትሎ እንዲሄድ ምክር መስጠትና ወደ ተገቢው መስመር እንዲገባ ማድረግ ተገቢ ነገር ነው። አጠቃላይ ነገሩን ገልብጦ እንዲህ ካልሆነ በቀደመው መንገድ ምላሽ እንሰጣለን የሚል አይነት ነገር ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ ፓርላማ ላይ እየተናገሩ የነበረው።

ያ የቀደመ መንገድ ምን ማለት ነው? ሲተችና ሲኮነን የነበረ መንገድ ነው። ነገር ግን በአጠቃላይ ይሄ ነገር በደንብ ቆም ተብሎ ካልታሰበ፣ በረዥም ሁኔታ ካልታየ በስተቀር በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ በችኮላ ለመፍታት ወደ እርምጃ መውሰድ ከተሄደ አሁን የታየውን ጭላንጭል ጨርሶውንም ሊያጠፋ የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው የሚመስለኝ።

ሚዲያው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ እንዴት እንዲንቀሳቀስ ይመክራሉ?

ዶ/ር አብዲሳ፡ ሚዲያዎች የራሳቸው ጠላት መሆን የለባቸውም። የተሰጠውን እድል አግባብ ባለው መንገድ መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው። በየክልሉና በተለያየ አይነት ብሔር ላይ እየተደራጀ የሚወጣው ሚዲያ በጣም በተመረጠ መንገድ ነገሮችን ቅርጽ የሚያሲዝበት መንገድ ከባድ ችግር ነው።

በአማራ ክልል የተከሰተውና አዲስ አበባ ላይ የሆነውን ነገር ፍሬም (የሚያቀርቡበት) የሚደረጉበትን መንገድ ብትመለከቺ በጣም ወገንተኝነት ባለው መንገድ ነው። ይሄ ራሱ ሚድያው ምን እየሆነ ነው የሚያስብል ነገር አለ። ትርክቶችን መፈተሽ [ቻሌንጅ] ማድረግ ተገቢ ነገር ሆኖ ግን ምሉዕ በሆነ መንገድ በትክክል ነገሮችን ህብረተሰቡ በሚረዳበት መንገድ ማቅረብ ነው የሚገባው።

ከአማራ ጋር የተገናኘ ሚዲያን ብትመለከቺ፤ በዳያስፖራ ያለውም ነገሮቹን ቅርፅ የሚያስይዝበት [ፍሬም] ፣ የመንግሥት ሚዲያም ለዚያ ምላሽ [ካውንተር] ለመስጠት እንደ “ጂሀዳዊ ሀረካት” የሚመስል አይነት ሪፖርት ማቅረብም ጀምሯል፤ አስደንጋጭ ነገር ነው። በጣም ፈጣን በሆነ መንገድ የተገጣጠሙና ክፍተቶች የበዙባቸው በደንም በበሰለ መንገድ ያልቀረቡ ነገሮች ብዙ ቢተነተኑ መዓት ነገር ሊወጣቸው የሚችሉና ትዝብት ውስጥ የሚጥሉ ነገሮችንም እያደረጉ ያሉበት ሁኔታ አለ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ትልቅ ስህተቶች እየተፈጠሩ የሚመጡበት እድል ሰፊ ነው። ማህበረሰቡን በጣም ጽንፍ እያስያዘ ሊሄድ የሚችልበት፤ ሕዝቡም መንግሥት ላይም ሚዲያ ላይም እምነት እንዲያጣ፤ እርስ በእርሱም እምነት የሚተጣጣበት ነገር እየሰፋ እንዲሄድ የሚያድረግ ነው።

ሚዲያውም ሰከን ብሎ ያለውን ችግር፤ ባገኘው መረጃ ላይ ተነስቶ በይሆናል ከመሄድ ይልቅ ምሉዕ [ኮምፕርሄንሲቭ] ሁሉንም አቅጣጫ ያካተተ ነገር ማቅረብ በጣም የሚጠበቅ ነው።

የሆነውን እውነታ [ፋክትን] ተቀብሎ ግን ደግሞ ሊጠየቁ የሚገባቸውን ነገሮች አግባብ ባለው መንገድ ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው። ያለውን [ፋክት] እየካዱ [የሴራ ትንታኔን] እያገዘፉ የመሄዱ ጉዳይ መልሶ ጉዳት ሊያመጣ የሚችልበት ሁኔታ አለ።

መንግሥትም አሁን እንደሚንለው አካሄዱ ጠንከር ባለው መንገድ ወደ ድሮው እንዲያውም በባሰ ሊሄድ የሚችልበት እድሎች ሰፊ ናቸው። አገርን ለመታደግ ነው በሚል [ዲስኮርስ] በዚህ መንገድ ሊቀጥል ይችላል። ራስን መጠበቅ የመንግሥት የመጀመሪያው ደመ ነፍስ ነው ስለዚህ ራስን ለመጠበቅ በሚወስደው እርምጃ ምንም ነገር የሚመርጥ አይደለም የሚሆነው። ስለዚህ ሁሉም ወገን በሰከነ መንገድ ኃላፊነት በተሞላው መንገድ ሊንቀሳቀስ ይገባል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US