ሲፒጄ ለኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች መስጋቱን ገለጸ

BBC Amharic : ኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የመገናኛ ብዙሃንን የመቆጣጠርና ጋዜጠኞች የማሰር ሁኔታ ቀድሞ ወደነበረው ጭቆና እንዳይመለስ ስጋት እንዳለው ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፒጄ ባወጣው ሪፖርት አመለከተ።

ሲፒጄ “ለውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ፕሬስን ለመቆጣጠር አሮጌውን ዘዴ እየተጠቀመች ነው” በሚል ባወጣው ሪፖርት የኢንትርኔት አገልግሎትን ማቋረጥና ጋዜጠኞችን ማሰርን እንደምክንያትነት ጠቅሷል።

የሲፒጄ አርማ

ሰኔ 15 አማራ ክልል ውስጥ ተሞከረ የተባለውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የኢንትርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉና ሲፒጄ ጨቋኝ ነው ባለው የጸረ ሽብርተኛነት ሕግ አማካይነት ቢያንስ ሁለት ጋዜጠኞች መታሰራቸው ከግንቦት ወር ወዲህ እየታየ ያለ ክስተት መሆኑን አመልክቷል።

ከኢንትርኔት መቋረጥ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ወራት ባለስልጣናት በርካታ ጋዜጠኞችን እንዳሰሩ የጠቀሰው ሲፒጄ ሐምሌ አንድ ደግሞ የመከላከያ ሚኒስቴር “በሠራዊቱና በሕዝቡ መካከል አለመተማመንን በሚፈጥሩ ባላቸው ግለሰቦችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ክስ ለመመስረት እንዳቀደ መግለጹን ጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ይገኛሉ ያላቸውንና ቀደም ሲል የታሰሩ ጋዜጠኞችን በሪፖርቱ ላይ በስም የጠቀሰው የሲፒጄ ሪፖርት በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተም በጋዜጠኝነት የተሰማሩና ለሙያው ቅርብ የሆኑ ሰዎች የተፈጠረባቸውን ስሜት አካቷል።

መንግሥት ከቆየው ልማዱ ለመላቀቅ እየታገለ ወይም በጋዜጠኞች ላይ አዲስ ዙር ጥቃት እየከፈተ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስ በርካታ ጋዜጠኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ይህ ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የወደፊት ዕጣ ፈንታን አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ሲፒጄ ምላሽ እንዲሰጡት ያናገራቸው የመንግሥት ቃል አቀባይ ስለታሰሩት ጋዜጠኞች ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረው ነገር ግን ተሞክሯል ከተባለው መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ላይ ባለስልጣናት ምርመራ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቢለኔ ስዩም በተወሰኑ የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ ላይ አስተያየት ያልሰጡ ቢሆንም ግን የታሰሩ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ሁሌም ከሥራቸው ጋር በቀጥታ የተገናኘ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ መንግሥት ለመገናኛ ብዙሃን በከፍተኛ ደረጃ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን እንደገለጹ ሲፒጄ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US