“ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው” አሊ ቢራ

BBC Amharic : በቅርቡ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለአንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ የክብር ዶክተሬት ሰጥቷል። አሊ ቢራ ለዓመታት ባስደመጣቸው ነጻነትና ፍቅርን በሚሰብኩ ሙዚቃዎቹ ይታወቃል። ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ማግኘቱን ተከትሎ ከአረንቀሎ ባንድ እስከ ዛሬ ስላለው የሙዚቃ ጉዞ ከቢቢሲ ጋር አጭር ቆይታ አድጓል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶሃል፤ ምናልባት የትውልድ ቦታህና ሙዚቃ የጀመርክበት ስለሆነ የተለየ ስሜት ነበረው?

አሊ ቢራ፡ ይሄ ከሰዎች የምሰማው ነው እንጂ ለኔ ለየት ያለ ክብርና ደስታ የተሰማኝ አለመሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ። ምክንያቱም ጅማም፣ ጎንደርም ሆነ ጎጃም የትኛውም ያከበሩኝ ቦታ አንዱን ካንዱ አብልጬ አይደለም የማየው ማለቴ ነው። አንድ ፎቶ ከብዙ ሺ ቃላቶች የበለጠ ራሱን ይገልፃል ይባላል። እጄን ዘርግቼ የተነሳሁትን ፎቶግራፍ አይተው፤ ከጅማ ዩኒቨርስቲ የበለጠ ደስታ እንደተሰማኝ አድርገው ሲያወሩ ነበር፤ እኔ የሚሰማኝ ሁለቱም እኩል ነው ያከበሩኝ፤ እግዚአብሔር ያክብራቸው። እጁን ስለዘረጋ የተለየ ደስታ ያሳያል የሚለውን ነገር አላውቅም።

ከዚህ ቀደም የክብር ዶክትሬት የሰጡህ ዩኒቨርስቲዎች የትኞቹ ናቸው?

አሊ ቢራ፡ ዩኒቨርስቲዎች አይደሉም፤ አንድ ዩኒቨርስቲ ነው። የጅማ ዩኒቨርስቲ ነው ያከበረኝ፤ እግዚአብሔር ያክብራቸው። ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ነበር የሰጡኝ፤ ሁለተኛው ያው ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ በቅርቡ የሰጠኝ ነው።

እስቲ ወደ ኋላ ልሂድና በ14 መትህ አረንቀሎ የሚባል ባንድ መስርተህ ነበር፤ በወቅቱም የተወሰኑ ሰዎች ታስረዋል። አንተም ተሰደህ ነበር፤ በሙዚቃውም በትግሉም የመጣህበትን ጉዞ አጫውተን

አሊ ቢራ፡ መጀመሪያ የመጣሁት ከአሥራ አራት ዓመት በፊት ነው። ይህም ከብዙ ዓመት ስደት በኋላ ነው። አሁን ሙሉ በሙሉ ከተመለስኩኝ አምስት፣ ስድስት ዓመት ሆኖኛል። በአፍረንቀሎ ባንድ ውስጥ ከመስራቾቹ አንዱ ነኝ እንጂ መስራች አይደለሁም። በእድሜ ከነሱ አነስ እላለሁ። አፍረንቀሎን ከመሰረቱት ውስጥ አሊ ሸቦ የሚባል እሱም ከሃረማያ ዩኒቨርሰቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል። እኔ ከነሱ ጋር ተቀላቅዬ አፍረንቀሎን መሰረትኩ። ስሜቱ በጣም ትልቅ ደስታን ይሰጣል በተለይም ባሁኑ ጊዜ ስናየው።

ባንዱ የተመሰረተው ከ57 ዓመት በፊት ነው። ባንዱ የነበረው ራዕይ ለተነሳው ትግል [ማለትም]፤ በዛን ጊዜ ማንነታችን፣ ኦሮሞነታችን፣ ቋንቋችንና ህልውናችን ተደምስሶ በነበረበት ወቅት ነው። እኛም ታግለን እንትን እናደርጋለን በማለት ተነስቶ፤ እንግዲህ የዛሬ 57 ዓመት ፍሬ እያፈራ፤ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል እየታየ፤ ዛሬ እንግዲህ ፈጣሪ ይመስገን ብሔር ብሔረሰቦች እኩል የሆኑበት፤ ሁሉም የየራሱን ማንነት እያስከበረ የሚኖርበት ዘመን ተፈጥሯል። የአፍረንቀሎ መነሻውና መድረሻው በጣም የሚያስደስት ነገር ነው። ነገር ግን ከብዙ መራራ ትግል በኋላ ነው። እስር፣ ግድያ ነበረው፤ ያው እዚህ ጋ መድረሳችን ተመስገን የሚያስብል ነው።

አባ ለፋ የሚለው አልበምህን ዶሚኖ ሬከርድስ የሚባል ኩባንያ ሙዚቃህን ለማተም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ሙዚቃውታተመ?

አሊ ቢራ፡ አዎ ታትሟል። የመጀመሪያ እትም በዚሁ በአገራችን ስፖንሰር የሚያደርጉት አኬፋ የሚባል ኩባንያ እዚሁ አትሞታል። ሌላኛው ደግሞ የድሮ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን እንደነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ማህሙድ አህመድ፣ አለማየሁ እሸቴ የመሳሰሉት የታተሙበት ኢትዮፒክስ (ቡዳ ሬከርድስ ) አትሞታል።

አባ ለፋ የራሱ ታሪክ አለው። ከነበረው የመሬት ከበርቴዎች ሥርአት በሕዝቡ ላይ ያደርሱ የነበረው ‘አትሮሲቲ’ [ግፍ] ለማስቀረት የሚደረግ ነው። መልዕክቶቹ ለሕዝቡ፣ ለአራሹ፣ ለተማሪውና ለሠራተኛውም የሚሆን ነው። ጊዜውን ጠብቆ ነው ያ ዘፈን የተዘፈነው። ወደ ዶሚኖ ልመለስና መጀመሪያ ጠይቀው ነበር። ቀጥታ ከኛ ጋር ሳይሆን ኢትዮፒክስን ከሚያሳትመው ከቡዳ ሬከርደስ ጋር ተነጋገሩ ብለናቸው ነበር። በኋላ ላይ ምን ላይ እንደደረሰ አላውቅም፤ ዝርዝሩን ባለቤቴ ነች የምታውቀው።

በኦሮምኛ ቋንቋ ብትዘፍንም ብዙው ኢትዮጵያዊ መልዕክቱን ቢረዳውም ባይረዳውም ሙዚቃህን ያውቀዋል። እንዲህ ቋንቋን አልፎና ትውልድን የሚያገናኝ ሙዚቀኛ ከመሆንህ አንፃር፤ ሙዚቃህ ያለውን ተፅእኖ እንዴት ታየዋለህ?

አሊ ቢራ፡ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። ንፁህ ሆኖ ለሀቅና ለትክክል የሚሠራ ሰው እግዚአብሔርም ከላይ ሆኖ ያየናል፤ ምድርም ጭንቅላት ያለውን ሰው ይረዳል። እኔ በሙዚቃዬ አቀነቅን የነበረው ስለ ሀቅ፣ መብትና ሰላም ነው። አንዳንዱ በኦሮምኛ ስለዘፈንኩኝ እንዴት በሶማሊኛ አልዘፈነም? ብሎ ሶማሌውን እኔ ላይ የሚያነሳሳ ሊኖር ይችላል። አማርኛ፣ እንግሊዝኛና ሌሎችም ቋንቋዎች [አሉ]. . . ቋንቋው ኦሮምኛ ይሁን እንጂ መልዕክቱ ዓለም አቀፍ ነው። በሰው ልጅ ላይ የሚደርስ ግፍ፣ ጭቆና፣ ሞት በየትኛውም አገር አለ። በኦሮምኛ ቋንቋ ስለተዘፈነ ወደ ኦሮምኛ ብቻ ጥግ የሚያስይዙኝ አሉ። ግን እኔ የማውቀውና የማስበው የሰውን ልጅ መብት መጋፋት እግዚአብሔር አላደረገውም፤ የሰው ልጅ ነው የሚያደርገው።

አካሄዴ፣ መነሻና መድረሻዬ በዛ ላይ የተመሰረተ ነው። ሙዚቃው ከሌላ ሙዚቃ የተሻለ ተብሎ አይደለም። ሰው ‘ሪዲንግ ቢትዊን ዘ ላይን’ የሚሉት አለ አይደል? [ግጥሞቼ በመሀል የማይታዩና የማይነበቡ መልዕክቶች አሉት]። እናም ቀና የሆኑ ሰዎች ሙዚቃዬን ይሰሙታል ቀና ያልሆኑ ሰዎች አንድ ጥግ ሊወስዱኝ ይችላሉ እንደ ማለት ነው። የኔ ፈጣሪ ተመስገን፤ ሁሉም ሰው ሙዚቃዬን እንዲወድልኝ እወዳለሁ። ይሆናል ብየም ሳይሆን፤ ስለ መሬት አራሹ፣ ስለ መብት፣ ስለ አካባቢም ከዘፈንኩ ከልቤ ነው፤ ለበጎም ነው። እናም በጎ አስተሳሰብ ያለው ሰው እየሰማ ያደንቅልኛል። ሌላውም እንዳልኩት በሆነ መንገድ ጥግ ሊወስዱኝ የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ለኔ የፈጣሪ ፀጋ ነው ሙዚቃዎቼ እንዲወደዱ ያደረገልኝ። ዋናው መልዕክቱ ነው።

ለምሳሌ በኦሮምኛ “ሲን ጃለዳ” ካልኩ በአማርኛ እወድሻለሁ ማለት ነው። በእንግሊዘኛ “አይ ላቭ ዩ” ማለት ነው። በኦሮምኛ “ሲን ጃለዳ” ስለሆነ በሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም አይችልም ማለት አይደለም። ተተርጎሞ ‘ግሎባል’ [ዓለም አቀፍ] ይሆናል። በፈረንሳይኛ፣ በቻይንኛም ይሁን በፈለገው ቋንቋ እወድሻለሁ እወድሻለሁ ነው። አንድ ጊዜ አፍረንቀሎ ውስጥ ሳለን ሳንሱር ተደርጎ ነበር። ዘፈን በአማርኛ ተርጉሙና አምጡ ተብለናል። እኛ ማታ ለኮንሰርት ተዘጋጅተናል። እና ሁሉንም ነገር (ወደ 30 ዘፈን) በአማርኛ ተርጉሙ ተባልን።

በኦሮምኛ “ጃለላ” ፍቅር ማለት ነው። ዘፈኑ ውስጥ ለአንዲት ልጅ ወይም ለፈለገው ነገር ፍቅር ሊኖረው ይችላል። ሰውየው “ጃለላ” ማለት ምንድን ነው? ሲለኝ ፍቅር ነው እላለሁ። ‘አዎ፤ [ፍቅር ማለት እንደሆነ] እናውቃለን፤ ግን እናንተ የምትሄዱበት መንገድ ይህ ፍቅር ምን አይነት ነው?’ አለኝ። ይታይሽ እንግዲህ አንድን ቃል በሁለት ቦታ ለመክፈል አይደለም “ጃለላ” የተባለው። “ጃለላ” ፍቅር ነው። የእናት፣ የአባት፣ የአገር [ሊሆን ይችላል]። ሙዚቃ መልዕክቱን ለሰው የሚያደርሰው የአንድ ቋንቋ ብቻ ሆኖ አይደለም። የዓለም ነው። በጎም መጥፎም ቢሆን። ሁሉም ቦታ ስላለ [ነው]።

አሊ ቢራ ታሪክ ነጋሪ ነው፣ ሙዚቀኛ ነው፣ የነጻነት ታጋይ ነው ይሉሀል አንተስ ራስህን ምን ብለህ ነው የምትጠራው?

አሊ ቢራ፡ እኔ ተማሪ ነኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን ምድር ላይ ወደ 7 ቢሊዮን ከምናምን ተማሪዎች አሉ። ከነዛ መሀል አንዱ ነኝ። ራሴን የማየው በዛ አይነት መንገድ ነው። ዛሬም እማራለሁ፤ ነገም እማራለሁ፤ ትላንትም ተማርኩኝ። ፈጣሪ በመዘነው አይነትና በሰጠኝ ያችን ብቻ ነው የማውቀው። እንጀራ እንጀራ ነው። ዳቦ ዳቦ ነው። እንደዚህ እንደዚህ ብሎ ከዚህ በላይ ከፍ እያለም የማውቀው ነገሮች አሉ። ስለ ትምህርት ከሆነ እድለኛ አይደለሁም። እንደ ብዙሀን የአገራችን ተጨቋኞች እና የደሀ ቤተሰብ ልጅ ስለሆንኩኝ እስከዚህም የመማር እድል አላገኘሁም። ግን በየቀኑ ትምህርት ቤት ሄጄ የምማረው ነገር አለ። ትምህርት ቤት ሲባል ጊቢ ሳይሆን አገር በሙሉ፣ ዓለም በሙሉ ትምህርት ቤት ስለሆነ ነው። እኔ የዓለም ተማሪ ነኝ። አንቺም፣ እሱም፣ እሷም ሁሉም [ተማሪ ነው]። በቀላሉ ራሴን የምገልጸው እንዲህ ነው።

የነጻነት ታጋይ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ለሚሉህስ?

አሊ ቢራ፡ ያ የተመልካቹና ስለኔ የሚያወራ ሰው የሚያውቀውን ነው የሚያወራው። ታጋይ መሆኔን ወይም እምቢተኛ ከሆንኩኝ የሰው ትርጓሜ ነው። ስለ አሊ ቢራ የዛ ሰው ትርጓሜ ነው። ስለዚህ እኔ ሰዎች አሁን እንዳልሽኝ ታጋይ ነው ሲሉ፤ እርግጥ ታጋይ ማለት ትልቅ ነገር ነው። ስለ ሀቅ የሚታገል ከሆነ። እኔ የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው ራሴን የምፈርጀው። አንዳንድ ሰዎችም እንደዛ ይሉኛል። በተቃራኒውም የሚሉኝም አሉ። የሀቅ፣ የመብት፣ የሰላም፣ የበጎ ነገር ታጋይ ነኝ እላለሁ።

አሁን ምን እየሠራህ ነው? ሙዚቃ አቁመሀል? ትዘፍናለህ?

አሊ ቢራ፡ አሁን ጡረተኛ ነኝ። በጥበብ ዉስጥ 57 ዓመት ሳገለግል ነበር። እግዚአብሔር በሰጠኝ ‘ኢነርጂ’ [ጉልበት] ተጠቅሜበታለሁ። እስካሁን ድረስ ፈጣሪ ይመስገን ብዬ። ከዚህ በኋላ እንግዲህ ብዙ ወጣቶች አሉ። ብዙ ታጋዮች አሉ። ብዙ ስለ መብት የሚከራከሩ አሉ። አሁን ‘ሪላክስ’ አድርጌ [ዘና ብዬ] እንደ ‘አድቫይዘር’ [አማካሪ] ሆኜ ለወጣት ሙዚቀኞች የማውቀውን አካፍልለሁ። የበለጠ ጊዜዬን [የማሳልፈው በዚህ ነው]። እናንተ ወጣቶች እንድትጦሩን ብዬ ነው። ግን አልፎ አልፎ ትልልቅ ኮንሰርቶች ባሉበት ጊዜ እታደማለሁ። አንድ፣ ሁለት እዘፍናለሁ እንጂ ‘ፕሮፌሽናሊ’ [እንደ ሙያ] እንደ በፊት ሙዚቃ ሠርቼ እኖራለሁ የሚለውን በቃ አቁሜያለሁ።

የጤናህስ ሁኔታ እንዴት ነው?

አሊ ቢራ፡ ጤናዬ የተጠበቀ ነው። በብዙ ዶክተሮች። ባለቤቴ የኔ ዶክተር ነች። ባለቤቴ አለ አይደል ወደ ሆስፒታል ትልከኛለች። የእድሜ ነገር ነውና ስኳር፣ የደም ግፊት ምናምን ነገሮች አሉ። እሷ መድሀኒቶቼን አስተካክላልኝ. . . ተቀጥራ የምትሠራ ነርስ ይመስልሻል። በጣም ጎበዝ ስለሆነች። ፈጣሪ ይመስገን እሷ ትረዳኛለች። በቃ በተቻለኝ መጠን ከፈጣሪ የሚሰጠኝን ጸጋ እየተቀበልኩ መኖር ነው።

እንግዲህ ለ56 ዓመት ዘፍነሀልና ላንተ ለየት ያለ ዘፈን የምትለው የትኛውን ነው?

አሊ ቢራ፡ እኔ ‘ኮምፖዝ’ ያደረኳቸው [ያቀናበርኳቸው] 267 ዘፈኖች ናቸው። ሁሉም የኔ ልጆች ናቸው። እኔ ልጆችም የሉኝም። ያለኝ 267 ዘፈኖች ናቸው። እና ከነሱ የትኛውን ትመርጣለህ? ቢባል በየጊዜው የራሳቸው ስሜት አላቸው። ስሠራቸው የሚሰማኝ ስሜት። ስለ ፍቅር፣ ስለ ቆንጆ ልጅ፣ ከዘፈንኩ በዛን ጊዜ የተሰማኝ ስሜት አለ። ስለ ‘ኢንቫይሮመን’ት [አካባቢ] ከዘፈንኩ በዛ ጊዜ ስለዘፈንኩት የሚሰማኝ ስሜት አለ። ስለ ፖለቲካም ከዘፈንኩ [እንደዛው]። እውነቴን ነው። ብዙ ሰዎች ይጠይቁኛል. . . ለዚህ ጥያቄ ግን የኔ ‘ፌቨራይት’ [ምርጥ] ይሄ ነው የምለው የለኝም። 267ቱንም በደንብ እንወዳቸዋለን። ለአድማጭ ‘ሪፈር’ የማደርገውም [የምጋብዘውም] 267ቱን ነው።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV ON YOUTUBE