ያሸነፈ መስሎት ሩጫወን በማቆም ደስታውን ሲገልጽ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ሃጎስ

አትሌት ሃጎስ ገ/ሕይወት

BBC Amharic : ባለፈው አርብ በስዊትዘርላንድ በተደረገው የዳይመንድ ሊግ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር አንድ አስገራሚ ነገር ተከስቷል።

ውድድሩን በሰፊ እርቀት ሲመራ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ሃጎስ ገብረሕይወት ገና አንድ ዙር እየቀረው ጨርሶ ያሸነፈ መስሎት ሩጫወን በማቆም ደስታውን ሲገልጽ ከኋላ በነበረው ዮሚፍ ቀጄልቻ ተቀድሟል።

አትሌት ሃጎስ ”የጨረስኩ ነው የመሰለኝ፤ ምን እንደተፈጠረ አልገባኝም። ይህ የህይወቴ ትልቁ ገጠመኝ ነው” ሲል ለቢቢሲ ስለሁኔታው ተናግሯል።

የ25 ዓመቱ አትሌት ሃጎስ ገ/ሕይወት በአትሌቲክሱ ልምድ ካላቸው የወቅቱ አትሌቶች መካከል የሚጠቀስ ነው። በሪዮው ኦሊምፒክ በ5 ሺህ ሜትር የነሃስ ሜዳልያ ባለቤት ሲሆን በዓለም ሻምፒዮና በርካታ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም ሃጎስ በሃገር አቋራጭ እና በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ድልን ተጎናጽፏል፤ ዓርብ ዕለት ያጋጠመው ግን ለእርሱም ትንግርት ሆኖበታል።

ሃጎስ ውድድሩን እንደማሸንፍ ”በእራሴ ተማምኜ ነበር። ስሜት ውስጥ ገብቼ ነበር። የሆነው ነገር ለእኔም ግራ ገብቶኛል” በማለት የተፈጠረው ነገር ለእርሱም ጥያቄ አንደሆነበት ደጋግሞ ተናግሯል።

“ሰው ሲደግፈኝና ሲያበረታታኝ፣ ጭብጨባውም ሲደምቅ ውድድሩን የጨረስኩ መሰለኝ። ከዚያ ሩጫውን አቋረጥኩት” ብሏል አትሌቱ።

ሃጎስ አንድ ዙር እየቀረው ያሸነፈ መስሎት ደስታውን እየገለጸ ሳለ የውድድሩን ዳኞች እና ከመሮጫ ትራኩ አቅራቢያ ያሉ ሰዎች ውድድሩ እንዳላለቀ ሲነግሩትና እሱም የተቀሩት ተወዳዳሪዎች ሩጫቸውን መቀጠላቸውን ሲመለከተ ነው እንደገና ወደ ሩጫው የተመለሰው።

በዚህ ምክንያት በቅርብ እርቀት ሲከተለው የነበረው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ አንደኛ ሆኖ ሲጨርስ ሃጎስ የአስረኛ ደረጃን ይዟል።

”ውድድሩን ያሸነፈውን ዮሚፍ ቀጄልቻን እንኳን ደስ ያለህ ብዬዋለሁ። አሰልጣኞቹም ‘ሊፈጠር የሚችል አጋጣሚ ነው’ በማለት አበረታትውኛል” ብሏል ሃጎስ።

“ቢሳካልኝ አሪፍ ነበር፤ አልተሳካም፤ በጸጋ መቀበል ነው” ሚለው ሃጎስ ከክስተቱ በኋላ በርካታ የስልክ ጥሪዎች እየደረሱት እንደሆነ እና አብኛኛዎቹም ”አይዞህ በርታ የሚያጋጥም ነው” የሚሉ ናቸው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በቀጣይ ሁለት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ይቀሩኛል የሚለው ሃጎስ፤ ለእነዚህ ውድድሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ልምምድ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።