በትግራይ የበሰል ምርት ላይ አደጋ ተጋርጧል ተባለ

BBC Amharic : ያለ በቂ ጥናት በችኮላ እንዲገባ የተደረገው የበለስ ትል ከጥቅሙ ይልቅ ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ራስ ምታት ሆኗል፤ በተለይም የደቡባዊ ትግራይ ያሉ ገበሬዎች የክልሉን መንግሥት ይራገማሉ።

ትሉ በክልሉ ያለውን የበለስ ምርት ሲያጠፋ ገበሬው መዓት ወረደብን ነው ያለው። ገበሬው ”የበለስ መዥገር” ብሎ የሚጠራውን ይህ ትል እስካሁን መፍትሔ አልተገኘለትም። መንግሥትም መድሃኒት ፍለጋ ከመባዘን ውጪ አንዳች ያገኘው ነገር የለም።

በለስ

ትሉ ወደ አገር ቤት እንዲገባ የተደረገው ህዝቡን ይጠቅማል ተብሎ ነበር። በመጀመርያ አካባቢ ጥቅሙ በተግባር ታይቷል፤ ገበሬዎች ትሉን በኪሎ እስከ 40 ብር መሸጥ ጀምረውም ነበር።

ኮችኔል (የትል) ወደ ትግራይ የገባው በአንድ ቺሊያዊ ኢኮኖሚስት ከ10 ዓመት በፊት ነበር። 60 በመቶ የፔሩ እና የሜክሲኮ ገበሬዎች ትሉን በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ እንደሚተዳደሩ ይነገራል። አንድ ኪሎ ኮችኔል እስከ 40 ዶላር ስለሚያወጣ ”ወርቅ የሆነ ትል ነው” ይሉታል።

በትሉ ውስጥ የሚገኘው ቀይ ቀለም ”ካርኒክ አሲድ” የሚባል ንጥረ ነገር የያዘ ነው። ይህ ንጥረ ነገር ወይንና ቪኖን የመሳሰሉ መጠጦች ቀይ ለማድረግ ይጠቅማል። በተጨማሪ ማርጋሪን እና ማርማላት፣ ኬክና በርገር፣ ሊፒስቲክና የጥፍር ቀለም እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ለመስራት ያገለግላል።

ሆኖም ከቁጥጥር ውጪ በመሆኑ ላለፉት በርካታ ዓመታት በለስ ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል።

ትሉ በባህሪው በቀላሉ በንፋስ የሚበተን እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም በፍጥነት ሊዛመት ችሏል። ደቡባዊ ዞንን አዳርሶ እንደርታ የገባ ሲሆን አሁን ደግሞ በዓጋመ ጋንታ አፈሹም በመከሰቱ ትልቅ ጭንቀት ፈጥሯል።

ምርመሩ የት ደረሰ?

በ2008 ዓ.ም ትሉ ደቡባዊ ዞንና እንደርታን አልፎ ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች እንዳይዛመት በክልተ አውላዕሎ እና ደጉዓ ተንቤን የማገጃ አካባቢ ተብሎ ተከልሎ ነበር።

ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና የክልሉ የእርሻ እና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊነት ወስደው ነበር። ነገር ግን ትሉ ወደ ወረዳዎቹ ከመግባት ያገደው ነገር የለም።

የአዲግራት የበለስ ምርምር ተቋም ሐላፊ አቶ የማነ ካሕሳይ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ”ትሉ እንከላከለዋለን ካልንበት አካባቢ አልፎ ቢገባም ከቁጥጥር ውጪ ግን አይደለም። እንዳመጣጡ ቢሆን ኤርትራ ይደርስ ነበር” ይላሉ።

”በለስ በአንድ ዓመት ውስጥ መጥፋት ይችል ነበር። ነገር ግን ከህብረተሰቡ ጋር ባደረግነው ጥረት ብዙ አደጋ አድርሷል ማለት አንችልም። ስለዚህ ከቁጥጥር ውጪ አይደለም ብለን ነው የገመገምነው” በማለት አስረግጠው ይናገራሉ።

ምርምሩ ሲጀመር ትሉን የሚያጠፋ መድሃኒት ተገኝቷል ተብሎ ነበር። እስካሁን ግን ጥቅም ላይ የዋለ የለም። እስካሁን ተቋሙ ትሉን ለመከላከል ያበረከተውን አስተዋጽኦን በተመለተ፤ የሚረጭ መድሃኒት እንደመፍተሄ እንዳልተወሰደ እና የተሻለው ከብራዚል በተገኘ ተሞክሮ ትሉን መቋቋም የሚችል ዝርያ መትከል ላይ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይ መቀለ ዩኒቨርሲቲም በመኾኒ ትሉን የሚቋቋም ዝርያ የመትከል ሙከራ እያደረገ እንደሆነ ኃላፊው ይናገራሉ። ከዚህ ውጪ ትሉን ለማጥፋት የሚያስችል መድሃኒት ተገኝቷል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ጥቅም እንዳልሰጠ የሚገልጹት ኃላፊው፤ ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው አካላትና የውጭ በጎ አድራጊዎች ጋር እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የገበሬው ድርሻ ምንድን ነው?

‘እግዚኣብሔር ያመጣውን መዓት እራሱ ይመልሰወቅ” የሚሉ ገበሬዎች አሉ። አብዛኞቹ ደግሞ መንግሥት እራሱ እንዳመጣው እራሱ መፍትሄ ያምጣ የሚል አመለካከት አላቸው።

ዩኒቨርሲቲው ለአርሶ አደሮቹ ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል። ”አርሶ አደሩ በለሱን እንዴት መጠበቅ እንደሚችል ቀበሌ እና ወረዳ ድረስ በመሄድ ትምህርትና ስልጠና እንሰጣለን” ይላሉ አቶ የማነ።

አሁን እየተሰራ ያለው የመከላከል ሥራ እያንዳንዱ አርሶ አደር ሊሰራው የሚችል እንደሆነም ይናገራሉ።

በትግራይ ክልል የገጠር እና እርሻ ልማት የበለስ ትል መከላከል እና መቆጣጠር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መለስ አባዲ በበኩላቸው ትሉን ለመከላከል ከክልል እስከ ታች ድረስ ኮሚቴ እንደተቋቋመ፤ ነገር ግን ለችግሩ ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ የሚመራ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

”በወጣው እቅድ መሰረት ተባበሮ መስራት ላይ ችግር አለ” በማለት በተያዘው እቅድ እንዳልተሰራም ይናገራሉ። ”ሆን ተብሎ ትሉ እንዲዛመት የማድረግ እንቅስቃሴም እየተደረገ ነው” የሚል ስጋት እንዳለም ባለሙያው ይገልጻሉ።

ይህ የበለስ ምርትን ክፉኛ እየተፈታተነ የሚገኘው ትል በንፋስ እና በእንስሳት አማካይነት ነው በቀላሉ የሚዛመተው።


► መረጃ ፎረም - JOIN US