ክልል የመሆን ጥያቄ ችግሩ በሰላማዊ እና በጥንቃቄ ካልተያዘ አደገኛ ሊሆን ይችላል ተባለ

DW : በደቡብ ክልል የሲዳማ ሕዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ በመግባባት በስምምነትና በጥንቃቄ እንዲፈታ «ክራይሲስ ግሩፕ » የተባለዉ ዓለም አቀፉ የግጭቶች አጥኒና መፍትሔ አፈላላጊ ተቋም አስታወቀ። ችግሩ በሰላማዊ እና በጥንቃቄ ካልተያዘ አደገኛ ሊሆን ይችላል ሲልም አስጠንቅቆአል። የህወሃት ኢህአዴግ መንግሥት ከ 20 ዓመት በፊት ያዋቀረዉ የብሔር ፌደራሊዝምና የግዛቶች አከላለል፤ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የሚነገር ሲሆን፤ በተለይ የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የለዉጥ መንግሥት ከመጣ ወዲህ ጥያቄዎቹ በተለያዩ ቦታዎች እየተነሱ እና የግጭትም መንስኤዎች እየሆኑ መምጣታቸዉ ይታያል። የጥያቄዎቹ መነሻና መሠረት የቀድሞዉ ኢህአዴግ የክልል መንግሥታቱን ሲመሰርት፤ በራሱ ጥቅምና ፍላጎት እንጂ፤ የነዋሪዎቹን ሕዝቦች ፍላጎት፤ አስተዳደራዊ አመቺነትና አግባብነት፤ ያላገናዘበ በመሆኑ እንደሁ ይነገራል። ችግሩ ካለፈዉ መንግሥት የተወረሰም ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የሲዳማ ሕዝብ የክልል ጥያቄ በተለይ ባለፈዉ ሐምሌ ወር ደግሞ የሲዳማ ሕዝብና አስተዳደሩ ጥያቄያቸዉን አጠናክረዉ ለሚመለከተዉ ክፍል በማቅረብ መልስ ሲጠብቁ ቆይተዋል። የብራስልሱ ወኪላችን ዓለም አቀፉ የግጭቶች አጥኒና መፍትሔ አፈላላጊ ተቋም የኢትዮጵያን ተወካይ አነጋግሮ ዘገባ ልኮልናል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US