የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር በተመሳሳይ አንድ ግቢ ውስጥ እንዲኖሩ እየተሰራ መሆኑን ጠ/ሚ ተናገሩ

በሚቀጥለው በጀት ዓመት ድህነት እና የዋጋ ግሽበት ቅነሳ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል – ጠ/ሚ ዶክተር አብይ

(ኤፍ.ቢ.ሲ) በሚቀጥለው በጀት ዓመት ዜጎችን ወደ ስራ ማስገባት ድህነት እና የዋጋ ግሽበት ቅነሳ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

የሎጅስቲክስ ስርዓቱን በማዘመን ምርቶችን በመያዝ ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት የሚፈጥሩ አላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የዋጋ ግሽበትን ለመከለከል እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው የ2012 የፌደራል መንግስት በጀት ውይይት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።

ተጨማሪ የሃብት መንገድ ከተፈጠረ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ሀገሪቱ ምን ያህል ብድር እንዳለባት እና ምን ያህል እዳ ትከፍላላች የሚለው ጉዳይ ሳይሆን፥ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ምርትና በብድር የሚከናዎኑ ፕሮጀክቶች ሁኔታ መታየት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሲድያግ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው በመጠቆም ካምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ልዩነት ያለው መጠባበቂያ ክምችት መኖሩን አንስተዋል።

በብድር የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ የብድር መክፈያ ጊዜ መድረስ እንደሌለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መሰል ችግሮችን ለማስተካከል ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን እና ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን ጤናማ መሆኑን ጠቅሰው፥ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የውጭ ምርት ገበያው ላይ ጭማሪ በማስመዝገብ የአበዳሪ እና ረጅ ሀገራትን ታማኝነት ከፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ካላት ሃብት መካከል አንዱ የሆነውን የሰው ሃብት በአግባቡ መጠቀም ለኢኮኖሚው እድገት የራሱ ድርሻ እንዳለውም አውስተዋል።

በሚቀጥለው በጀት ዓመት ለ3 ሚሊየን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን በመግለጽም በሀገሪቱ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ወደ መካከለኛው ምስራቅና አውሮፓ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለመላክ መታቀዱን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም እንጅ እጥረት እንደሌለ በመጥቀስም 100 ሚሊየን ህዝብን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ሃብት ነው ብለዋል።

የሃይል እና ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦት ማሟላት በርካታ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በቀላሉ ለማፍሰስ እንደሚያስችልና የስራ እድል ከመፍጠር በተጨማሪ ለኢኮኖሚው እድገት ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በፖታሽ፣ ወርቅ፣ ጋዝና ሌሎች ማዕድናት ያላትን ሃብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

በተጨማሪም ብዙ የሚሸጥና ገቢ ማስገኘት የሚችል ያልታዩ ሀብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፥ በሚቀጥለው በጀት አመት አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ስራዎችን ለመስራት ታቅዷል ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር በተመሳሳይ አንድ ግቢ ውስጥ እንዲኖሩና የታችኛው ብሄራዊ ቤተ መንግስት ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በታችኛው ብሄራዊ ቤተ መንግስት በርካታ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቁሳቁሶች ተከማችተው የሚገኙ ሲሆን፥ በመዲናዋ ብቻ በርካታ ስራዎችን በመሰራት ሃብት ማፍራት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ይህም በርካታ የሃብት ፍሰት ወደ አዲስ አበባ እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US