በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተከሰተ ግጭት የ8 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በተከሰተ ግጭት የ8 ሰዎች ሕይወት አለፈ

(ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በተከሰተ ግጭት የ8 ሰዎች ሕይወት አለፈ።

የክልሉ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ እንደገለጹት፥ በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ገነተ ማርያም ቀበሌ ትናንት በተፈጠረው ግጭት የ8 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 11 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሶባቸው የህክምና ክትትል እያደረጉ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም ነው ሃላፊው የተናገሩት።

የግጭቱ መነሻ የገነተ ማርያም ቀበሌ ምክትል አስተዳዳሪ በጩቤ ተወግተው መሳሪያቸውን በመነጠቃቸው መሆኑን አቶ አበራ ተናግረዋል።

አሁን ላይም የተፈጠረውን ግጭት ለማረጋጋትና ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ 27 ያህል ሰዎች በዚህ ግጭት ህይወታቸው እንዳለፈ ተደርጎ የሚነዛው ወሬ ከእውነት የራቀ መሆኑን ሃላፊው መግለፃቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US