ለጀነራል አሳምነው ቀብር የላሊበላ ህዝብ በነቂስ መውጣቱ ተዘገበ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑት የብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሰኔ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በቤተ ጊዮርጊስ የቀብር ቦታ ተፈፅሟል።
ለስርዓተ ቀብሩም የከተማው ሕዝብ በነቂስ ወቷል።

የከተማው ነዋሪና የቀብር ሥነስርዓት አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አባይ ወዳጀ አስክሬኑ የእርሳቸው መሆኑን ሳጥናቸውን ከፍተው አረጋግጠዋል።
የጄኔራሉን አስክሬን አጅቦ የመጣ የመንግሥት አካል አልነበረም።
አስክሬኑ ከአውሮፕላን ማረፊያ ወደ ተዘጋጀለት ማረፊያ አደባባይ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ ያረፈ ሲሆን ሌሊቱን ሙሉ ፀሎተ ፍትሃት ሲደረግላቸው፤ ነዋሪዎችም ሃዘናቸውን ሲገልፁ አድረዋል።

ዛሬም ከተለያዩ አካባቢዎች በመኪና የመጡ ወጣቶችን ጨምሮ ፖሊስና ሚሊሻ፣ ከተማ አስተዳደሩ፣ ነዋሪዎች በጋራ በመሆን በደማቅ ሁኔታ ሥነ ስርዓቱን ለመፈፀም የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በተኩስ ከተማዋ ተናውጣለች [በሃዘን ወቅት በሚተኮስ ተኩስ]።
‘አሳምነው ፅጌ እንዲህ ዓይነት ድርጊት አይፈፅምም፤ ይጣራልን።
አማራ ክልል አንድነት እንዳይኖረው የተደረገ ሴራ ነው።
የታሰሩት እነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ይፈቱልን ”
የሚሉ መፈክሮች ሲሰሙ ውለዋል።

በአካባቢው እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ይነሱ እንጂ በከተማው የተፈጠረ የፀጥታ ችግር አልነበረም።
ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ ዛሬም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ነበሩ።
“ጄነራል አሳምነው ባለፈው ዓመት ለአሸንድዬ በዓል አከባበር ላሊበላ ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ ‘ከዚህ በኋላ የምኖረው ለአማራ ህዝብ ነው’ ብሎ ስለተናገረ ‘ አማራን ለማጥፋት የተደረገ ሴራ ነው’ የሚሉ ነዋሪዎች መንግሥትን እየኮነኑ፣ ጥይት እየተተኮሱ፤ በፉከራና ቀረርቶ ታጅቦ ሥነ ሥርዓቱ ተከናውኗል።

የቢቢሲ አማርኛ ዘገባን መሰረት በማድረግ የተጠናቀረ