ጉጂ ዞን በሁጡራ ዘመቻ የታጠቁ ቡድኖች በቁጥጥር ስር ዋሉ

DW ; የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ እንዳሉት በምዕራብ ጉጂና በደቡብ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የታጠቁ ቡድኖች የሚሄዱትን ኢሰብአዊ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችል ርምጃ ተግባራዊ አየተደረገ ይገኛል። የዞኑ መስተዳድር በታጠቁ ቡድኖች ላይ የጸጥታ ርምጃ እየወሰደ የሚገኘው ከአገር መከላከያ ሰራዊትና ከነዋሪው ህዝብ ጋር በመተባበር መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

ባላፉት ሦስት ቀናት ብቻ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ሁጡራ (ማፅዳት) በሚል በተካሄደ ዘመቻ እስከአሁን አንድ መቶ ሃያ የኦነግ ሸኔ ተጣቂዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ የገለፁት። በምዕራብ ጉጂ ዞንና በደቡብ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች አሁን የሚታየው የጸጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ እስከሚቀረፍ ድረስም በእሳቸው አጠራር የሁጡራ ዘመቻው ተጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በምዕራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ ሆቴሳ በበኩላቸው በአካባቢው በታጣቂዎች ላይ እየተወሰደ ከሚገኘው አርምጃ ጎን ለጎን የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የአገር ሽማግሌዎች ዛሬ የእርቅ ስረዓት ሲያካሂዱ መዋላቸውን ተናግረዋል።በተጨማሪም ላለፉት ሁለት ዓመታት በታጣቂዎቹ ተዘግተው የቆዩት የዲላና የቡሌሆራ ከተሞችን ከአማሮና ቡርጂ ወረዳዎች የሚያገናኙ መንገዶች ሰሞኑን ተከፍተው የትራንስፖርት አንቅስቃሴ መጀመሩን ነው ዋና አስተዳዳሪው አቶ ማቴዎስ ለዶቼ ቨለ (DW) በስልክ የገለፁት ።

የፖለቲካ ሳይንስ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያና የደቡብ ክልል መስተዳድር የፕሬስ ሴክሬቴሪያት ፅህፈት ቤት ከፍተኛ የስራ ሃላፊ የሆኑት አቶ ዳያሞ ዳሌ በበኩላቸው መንግስት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ መውሰድ የጀመረው ርምጃ ቀድሞወኑ ሲጠበቅ የነበር ነው ብለዋል።

መንግስት በምዕራብ ጉጂ ዞን በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ እየወሰደ ይገኛል በተባለው እርምጃ ዙሪያ እስከአሁን በኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኩል የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ መግለጫ የለም።
የምዕራብ ጉጂ ዞንን ከደቡብ ክልል የአማሮና የቡርጂ ወረዳዎች በሚያዋስኑ ስፈራዎች ታጣቂዎች በደፈጣ በሚያደረሱት ጥቃት እስከአሁን ከአምስት መቶ በላይ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ከየወረዳዎቹ መስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE