30ሺ የሚደርሱ ቤቶች ይፈርሳሉ መባሉን ተከትሎ ውጥረቱ መባባሱ ታወቀ

በአዲስ አበባ ቤቶች ይፈርሳሉ መባሉን ተከትሎ ውጥረቱ መባባሱ ታወቀ

(ኢትዮ 360 )

በአዲስ አበባ ወደ 30ሺ የሚደርሱ ቤቶች ይፈርሳሉ መባሉን ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ የተፈጠረው ውጥረት መቀጠሉ ተሰማ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የሚፈርሱት ቤቶች በ15 ቀናት ውስጥ በከተማዋ በህገወጥ መንገድ የተገነቡትን ነው ቢልም ነዋሪዎቹ ግን ሃቁ ሌላ ነው ሲሉ ለኢትዮ 360 ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በየወረዳዎቹ አመራሮች የተሰጠን መመሪያ ከ7 አመትና ከዛ በላይ የኖርንበት ቤታችንን በ15 ቀናት ውስጥ ራሳችን አፍርሰን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ ነው።አመራሮቹ ይሄን ሲሉም ህግ ህግ ነውና መከበር አለበት ስለዚህ ይሄንን ተግባራዊ እናደርጋለን ሲሉ ነው ለነዋሪዎቹ መመሪያ ያስተላለፉት።ክረምት ሲመጣ ተጠብቆ የሚካሄደው ቤት ማፍረስና ማፈናቀል በደሃው ህዝብ ላይ እንዲፈጸም የሚደረግበት አግባብ አይገባንም ይላሉ ነዋሪዎቹ።በተለይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤታቸውን እንዲያፈርሱ የተነገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት በአካባቢው በ15 ቀናትም ሆነ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የተካሄደ ህገወጥ ግንባታም ሆነ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የለም።


ይሄ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ቤታችሁን አፍርሱ የሚል መመሪያ መተላለፉ ህጋዊ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ ነዋሪዎቹ።ይሄን መመሪያ በደሃው ህዝብ ላይ የሚያስተላልፉ አመራሮች በሌብነት የተገነቡ ቤቶችን ለማስፈረስ ግን ስልጣናቸውን ሲጠቀሙ አይታዩም ሲሉ ይከሳሉ።በቅርቡ የፋብሪካ የምረቃ ስነ ስርአት ላይ የተገኙትን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማን ስለጉዳዩ አነጋግረናል የሚሉት ነዋሪቹ መመሪያው እናንተ የሚመለከት አይደለም፣በህገወጥ መንገድ በቤት ግንባታ ቤት በመሸጥና በመለወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ነው ሲሉ ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።


የተሰጣቸው የ15 ቀን ገደብ መጠናቀቁን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ በቀጣይ አመራሮቹ የሚወስዱትን ርምጃና የምክትል ከንቲባው ቃል ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል በሚለው ውጥረት ውስጥ መሆናቸውን ነው ለኢትዮ 360 የገለጹት።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE