ሪል፣ ሙኒት፣ ሳሚ፣ ሐርሚ፣ ሰናሚ እና ሳሮን የተባሉ የአቼቶ ምርቶች ህብረተሰቡ እንዳይጠቀም መንግስት አሳሰበ

የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ባላሟሉ ስድስት የአቼቶ ምርቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የአምራች ድርጅቶቻቸው አድራሻና ምንጫቸው የማይታወቁ የምግብ ምርቶች ገበያ ላይ እየዋሉ መሆኑን በተደረገው የገበያ ቅኝት ማረጋገጡን አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ድርጅቶች ተመርተው ወደ ገበያ በተሰራጩ ምርቶች ላይ በተደረገ የገበያ ቅኝት በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ያላሟሉ፣ ምንም ዓይነት ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸውና የአምራች አድራሻ እና መለያ ቁጥር የሌላቸው የአቼቶ ምርቶች ገበያ ላይ መገኘታቸው ተረጋግጧል።

ምርቶቹም ሪል፣ ሙኒት፣ ሳሚ፣ ሐርሚ፣ ሰናሚ እና ሳሮን የተባሉ የአቼቶ ዓይነቶች መሆናቸውም ነው የተገለፀው።

በምርቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የገለጸው ባለስልጣኑ፥ ህብረተሰቡ እነዚህን የአቼቶ ምርቶች እንዳይጠቀም ማሳሰቡን ከኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ምርቶች በሌሎች የመገበያያ ስፍራዎች ላይ ሲመለከትም በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ፣ ለፖሊስ አካላት ወይም በፌዴራል ደረጃ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ ስልክ መስመር 8482 በመጠቆም እንዲያሳውቅ ጥሪ ቀርቧል።

በተጨማሪም የክልል ተቆጣጣሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ የቁጥጥር አካላት ምርቶቹን ከገበያ ላይ በአፋጣኝ የመሰብሰብ ስራ እንዲሰሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE