የ2012 የመንግስት በጀት ከ2011 በ11.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል

የፌደራል የመንግሥት በጀት በአራት ዓመታት ውስጥም ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

BBC Amharic

በትናንትናው ዕለት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 71ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2012 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የፌደራል መንግሥት በጀት ረቂቅ ላይ ተወያይቶ፤ 386 ቢሊዮን 954 ሚሊዮን 965 ሺህ 289 ብር እንዲሆን ውሳኔ በማሳለፍ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።

ከዚህም ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 109 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ቢሊዮን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 140 ቢሊዮን እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ መመደደቡን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ይህ ለቀጣይ ዓመት የተያዘው ሃገራዊ በጀት ላለንበት 2011 ዓ.ም ከተያዘው ጋር ሲነጻጸር በ11.5 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፤ ከባለፈው 2010 ዓ.ም ጋር ደግሞ በ20.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ይህም በመጠናቀቅ ላይ ባለው ከ2011 ዓ.ም በጀት ጋር ሲወዳደር ከአርባ ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል። በዚህ በጀት ዓመት 346 ቢሊዮን 915 ሚሊዮን 451 ሺ 948 ተመድቦ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ለመደበኛ ወጪ 91 ቢሊዮን 67 ሚሊዮን 160 ሺ 588 ብር እንዲሁም ለካፒታል ወጪ 113 ቢሊዮን 635 ሚሊዮን 559 ሺ 980 ተመድቦ ነበር። ይህ በጀት በ2010 ዓ.ም ከፀደቀው አንፃር የ3.6 በመቶ ጭማሪ እንደነበረውም ተገልጿል።

በ2010 የነበረው በጀት 320.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ከ60 በመቶ የሚበልጠው ለትምህርት፣ ለግብርናና ለመሰረተ ልማትና ለጤና ማስፋፊያ እንዲሆን ተብሎ የተበጀተ ገንዘብ ነበር።

ከ300 ቢሊዮን ብር በታች የነበረው የኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት በ2009 ዓ.ም ላይ 274.3 ቢሊዮን በጀት ተመድቦ ነበር።

የፌደራል የመንግሥት በጀት በአራት ዓመታት ውስጥም ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀጣይ ዓመት የሃገሪቱ በጀትን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ ለሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል። ከዚህ በፊት ከነበረው ልምድ በመነሳት የቀረበው በጀት ያለችግር እንደሚጸድቅ ሲሆን ምክር ቤቱም የዓመቱን የሥራ ጊዜውን ከማጠናቀቁ በፊት የጨረሻው ውሳኔ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE