በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁ ክፍተት መረጃ የማይሰጡ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ አልተቻለም

ENA : የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጁ  ክፍተት ያለበት መሁኑ መረጃ የማይሰጡ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንዳልተቻለ የኢፌዴሪ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

አዋጁን ለማሻሻል ረቂቅ ጥናት ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተቋሙ ገልጿል፡፡

የህዝብና የግለሰብ ጥቅምን ለማስጠበቅ የወጡ ተገቢ ገደቦች እንደተጠበቁ ሆኖ ከማንኛውም መንግስታዊ አካል ዜጎች መረጃን የመጠየቅ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 ይደነግጋል፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ የመንግስት ተቋማት በሚዲያዎች መረጃ ሲጠየቁ በተለያየ ምክንያት መረጃዎችን በወቅቱ ያለመስጠት ይስተዋላል፡፡

ማንኛውም ሰው መረጃ የመጠይቅ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብት እንዳለው በአዋጁ ተቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ መረጃ በማይሰጡ አካላት ላይ ስለሚወሰድ እርምጃ በግልጥ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ  በአዋጁ ላይ ክፍተት እንዳለበት ነው በኢፌዴሪ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ዳይሬክቶሪት ዳሬክተር አቶ ማናየ አለሙ  የሚናገሩት ፡፡

የመንግስት ተቋማት መረጃዎችን በወቅቱ ያለመስጠት በስፋት እንዳለ የጠቆሙት ዳሬክተሩ መረጃ በወቅቱ በማይሰጡ አካላት ላይ ምን እርምጃ መወሰድ አለበት የሚል ረቂቅ ጥናት ተጠንቶ  ለሚኒስተሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

አዋጁ ዜጎች መረጃን የመጠየቅ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው ይደንገግ እንጂ ለሚዲያዎች በምን ያህል ጊዜ መረጃ መሰጠት እንዳለበት ለብቻው ተለይቶ አለመውጣቱ ደግሞ ሌላኛው አዋጁ ላይ ያለ ክፍተት ነው፡፡

ሚዲያው የህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 የተለየ ጥበቃ እንዲደረግለት ተቀምጧል፡፡

በመሆኑም ሚዲያዎች በአጭር ጊዜ መረጃዎችን ማግኘት እንዲችሉ  የሚዲያ ነፃነት አዋጅ ከመረጃ ነፃነት አዋጅ ውጭ ተነጥሎ  እነዲወጣ  በረቂቅ ጥናት መካተቱን ነው አቶ ማናየ የሚያስረዱት፡፡

መረጃ ጠያቂው አካል በተቋሙ የህዝብ ግንኙነት አማካኝኘት የጠየቀውን መረጃ ማግኘት ካልቻለ ለተቋሙ የበላይ አመራር በማቅረብ መረጃ ማገኘት ይችላል፡፡

ይህ ሳሆን ቢቀር ግን ከህዝብ እንባ ጠባቂ እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ ይግባኝ ማለት እንደሚችል በአዋጁ ተቀምጧል፡፡

ሂደቱ ግን ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ መረጃ ፈላጊው መረጃውን ለታለመለት አላማ በወቅቱ እንዳያገኝ ስለሚያደርገው ህብረተሰቡ በወቅቱ መረጃዎችን ማግኘት እንዲችል በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተቱንም ከኢፌዴሪ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE