ሕብረ- ብሔራዊነት መለያችን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቃችን

ሕብረ-ብሔራዊነት መለያችን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቃችን
የኢሕአፓ አባላት እናት አገራቸው ኢትዮጵያን በዝናና በታሪክ ብቻ ሳይሆን በሥልጣኔም ሆነ በዕድገትዋ ከዓለም ቀደምት ሀገሮች ደረጃ ለማድረስ፤ የሚወዱትና የሚያከብሩትን ታላቅ ሕዝብ ከድኽነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲሁም ፍትኅና እኩልነትን በሀገራቸው ለማስፈን ክቡር ዓላማና ብሩህ ተስፋን ሰንቀውም ነበር ለትግሉ የተነሱት፤ ወደትግሉም የገቡት። በአገር ሉዓላዊነትና በህዝባዊ ፍቅር ስሜትና እምነት መርህ ላይ ተሣሥረውና የተጠናከረ ሕብረ-ብሔራዊ ጥምረት ፈጥረው መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት የተሰለፉ ቆራጥ ጀገኖችም ነበሩ። ባጠቃላይም ከኢሕአፓ ውጪም ሆነ በኢሕአፓ ውስጥና በኢሕአፓ ዙሪያ ለየግል ጥቅማቸው ሳይሆን ላመኑባቸው ዓላማዎች በቅንነትና በቆራጥነት የተሰለፉት ታጋዮች በእርግጥም የመላው ሕዝብ ብርቅዬ ልጆች መሆናቸው ታሪክ የመሰከረላቸው ናቸው።

ለውጥ ፈላጊው ትውልድ፣ ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የተከፈለውን ከፍተኛ መሰዋእትነት በማድነቅና ተገቢውንም ክብር በመስጠት፤ ያለፉትን ጀግኖች ታሪክ አርዓያነት በመከተል፤ ከፊቱ የተደቀኑትን ነባር የሀገሪቱ ውስብስብ ችግሮች መፍታትና ህልውናዋ የተከበረ፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባትን አገር መገንባት ለነገው ትውልድ የማይተው የትውልዱ አደራ መሆኑን ጠንቅቆ የተረዳ ጀግና ትውልድ ነበር። የዚያ ትውልድ አባላት ከመፈጠራቸው በፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች የነበሩ ሲሆን የአገርና የወገን ችግር እጅግ ለሚያሳስበው ለዚያ ትውልድ አገራዊ አመለካከት መያዝም ሆነ ሆነ በወቅቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ መግባት የግድ የሚልበት ወቅት ነበር።

የዚያ ትውልድ የተማረ ክፍል የኢትዮጵያን ሁኔታ እንዴት መለወጥ እንደሚቻል አምርሮና አጠንክሮ መጠየቅ ሲጀምር ፤ የሀገሩን የቅርብና የሩቅ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመረዳት እድሜውና እውቀቱ የፈቀደለትን ከማየትና ከማገናዘብ ከመመርመርም አልፎ ለለውጥ ሲነሳ አንግቧዋቸው የነበሩት የዲሞከራሲና የመብት ጥያቄዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ (ከሊቅ እስከ ደቂቅ) ቀልብ የሳቡና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳታፉ ነበሩ። ጥያቄውና እንቅስቃሴውም፣ ለሥርዓት ለውጥ የተደረገ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንደነበር ፀሐይ የሞቀው ታሪክ የመዘገበው ሐቅ ነው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ/መረጃ የሚሆነው በ1966 ዓም የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ የኅበረተሰብ ከፍሎች እነማን እንደነበሩ መጥቀሱ ጠቃሚ ነው። እነሱም (1) ከገባርነት ለመላቀቅ የመሬት ጥያቄ መፍትሄ ይሻ የነበረው ገባሩ አርሶ-አደር፤ (2) ከመብት ጥያቄና ከማኅበር ምሥረታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያነሳው ላብ-አደር፤ (3) የጾታ እኩልነት ይከበር ብለው የተነሱት ሴቶች፤ (4) የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ አንስተው ሰልፍ የወጡ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች፤ (5) ሥርዓተ-ትምህርቱ እንዲሻሻል የጠየቁ መምህራን፤ (6) የደሞዝ ጭማሪና የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻልላቸው የጠየቁ ወታደሮች፤ (7) የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ የጠየቁ ታኪሲ ነጂዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ነበሩ።

የ1960ዎቹ ወጣት ትውልድ በወቅቱ በአገራችን ውስጥ ይታይ የነበረውን ፍፁማዊ የዘውድ አገዛዝና በዓለም ደረጃም ይታይ የነበረውን የቅኝ ግዛት አገዛዝን (በናሚቢያ፥ በዚምባቡዌ፥ በሞዛቢክ፥ በደቡበ አፍሪካ፥ በቬትናም፥ ….ወዘተ) በፅኑ ይቃወም ነበር። ትምህርትን፣ ሕክምናን፣ ሥራን፣ … ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ፤ የብዙኅኑን መብትና ጥቅም በእኩልነት የማስከበር፤ የመደብና የብሔር ጭቆናን አስወግዶ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ዕውን የማረግ ፤
ማኅበራዊ ፍትህን የማስገኘት፤ የሕዝብን ጥቅም መሰረት ባደረገ ፖሊሲ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የማምጣት ትልቅ ዓላማን አንግቦና ብሩህ ተስፋን ይዞ ነበር የተሰባሰበው፣ የተደራጀውና ለትግል የተሰለፈው። ይህ ክፍል ነው እነዚህን ክቡር ዓላማዎች በፖለቲካ ድርጅት መልክ ተደራጅቶ ለማራመድ የዛሬ አርባ ሰባት ዓመት በሚያዚያ 1964 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርነት ድርጅት (ኢሕአድ) የመሠረተውና በኋላም በ1967 ነሐሴ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በሚል ስም ለሕዝብ ራሱን ይፋ ያደረገው።

ኢሕአፓ ከመመሥረቱ በፊት ስለ አደረጃጀትም ሆነ ስለ ፖለቲካ ትግል በአርዓያነት ሊያገለግለው የሚችልና ተመከሮውንም በማገናዘቢያነት ሊጠቀምበት የሚችል ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት አልነበረም። በመሆኑም የኢሕአፓ ምሥረታ በሀገራዊ ፖለቲካና በመደራጀቱ መስክ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

ኢሕአፓ የተበደለውን ሕዝብ ብሶት ብሶቴ ብሎ በተደራጀ መልክ የሕዝቡን ችግሮች ለመፍታትና ጥቅሞች ለማስጠበቅ የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የወደፊት ሕይወት ለማሻሻልና ሀገሪቱ ካላቸበት ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ ቆርጦ መነሳቱና በቅንነት መታገሉ በማንም ሊታበልም ሆነ ሊካድ የማይችል ሐቅ ነው። ያ በኢሕአፓ ውስጥ ተሰባስቦ የነበረው ትውልድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀሳቡን የመግለፅና የመደራጀት መብት እንዲያገኝ፤ በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ተጭነው የነበሩት የመደብ፣ የብሔረሰብ፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ …ወዘተ ጭቆናዎች እንዲወገዱ በቅንነት ፈልጎና አስቦ አስፈላጊ መሠረታዊ ለውጦችን ለማምጣትም አልሞ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል በርግጠኝነት የተነሳና በተግባርም ራሱን አሳልፎ የሰጠ ትውልድ ነበር። ዛሬም ነው።

ኢሕአፓ በረዥሙና በመራራው የትግል ሂደት ለሕልውናው ማጠየቂያ የሆነውን የሀገርና የህዝብ ፍቅር ተንከባክቦ ያቆየ ሲሆን ፤ በጀግንነትና በመስዋዕትነት የጻፈውንም የአርባ ሰባት (47) ዓመት የትግል ታሪክ በዕውቀት ለማዳበር ችሏል። የኢሕአፓን አባላትና ደጋፊዎች ያገናኛቸው ያስታሳሰራቸውና የጠነከረ ውስጣዊ ውህደት እንዲኖራቸው የረዳው ከውስጣቸው ፈንቅሎ የሚወጣው የሕብረተሰቡን ብሶት የሚገልጡበት የሾለው ብእራቸው ሲሆን የጥንካሬ እሴቶቻቸውና ጉልበታቸው በብዕር መገንባታቸው ጭምር ነው። በዚሁ ብዕራቸውም ነበር የፍትህን፣ የዴሞክራሲን፣ የእኩልነትንና የሀገር ሉዓላዊነትን ብርሃን በሀገሪቱ ለማብራት ሲታገሉ ሁሉንም የኢትዮጵያ ልጆች በማሰባሰብ ባንድ ሀገራዊ ሰንደቅ ሥር ለማሰለፍ የቻሉት።
በኢሕአፓ ዙሪያ ተሰባስበው የታገሉት አባላቱ በጎጥ፣ በፆታና በኃይማኖት ሳይለያዩ፤ ከጠባብነትና ከትምክህት ተቃርነው፤ ለአምባገነኖችና ለባእዳን ሳይንበረከኩ በሕዝብ እኩልነት ምለው ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች የደስታ ቤት እንድትሆን ያመኑ እንጂ ዛሬ አንዳንድ የታሪክ በራዦችና ከላሾች ሊሉ እንደሚከጅላቸው ኢትዮጵያን ለመጉዳት ከኤርትራው ሻዕብያ፤ ከሱማሌው ዚያድ ባሬና፤ ከአረቦቹ ባጠቃላይ ከባእዳን፣ … ወዘተ ጋር አገራቸውን ለመጉዳት የተሰለፉም ሆነ የተሞዳሞዱ አልነበሩም። ኢሕአፓ የኢትዮጵያን ችግር በቅጡ የተረዳ ለችግሯም መፈወሻ መንገዱን (መድኃኒቱን) ያመላከተ እንጂ ለሄደ

ለመጣው አምባገነን ሁሉ ለጥቅም ፍለጋ በማጎንበስ በሽታዋን ያባበሰ አልነበረም። ይልቁንም ለሀገሩና ለወገኑ መድህን ለመሆን መስዋዕትነትን በፀጋ ለመቀበል የተዘጋጀ ትውልድ ነበር።

የዚያ ለውጥ ፈላጊ ትውልድ አባላት የዜጎች የእኩልነት መብት መከበርና የኢትዮጵያ ህልውና የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ጠንቅቀው በመረዳት አምርረው ታግለዋል። አምባገነኖች ጥያቄውን በነፍጥ ለመፍታት በማሰብ ያ ትውልድ ያቀረበውን አማራጭ በትጥቅ አስፈቺነት ፈርጀው በኢሕአፓም ላይ ዘምተዋል። ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሄድ ደርግ ያን ሰላማዊ መፍትሄ የሚሻ ድምጽ (ትውልድ) ማጥፋት እንዳለበት አምኖና አቅዶ በኢሕአፓ ላይ ቀይ ሽብርን አወጀ። መተኪያ የሌለውን አንድ ትውልድም መተረ።

የኢሕአፓን አገራዊና ሕዝባዊ ራዕይ የፈሩና በኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ባለው የጸና እምነትና አካሄድ ያልተመቻቸው እንደ ሻዕቢያ፥ ወያኔ፥ ኦነግና የሱማሌ አቦን የመሳሰሉ ብሔርተኛ ኃይሎች ለሚያራምዷቸው ጽንፈኛና የመገንጠል ዓላማቸው እንቅፋት ነው ብለው በማመናቸው ኢሕአፓን እንደጠላት ቆጠሩት። የኢትዮጵያ የእኩልነት ጥያቄ በሰላማዊና ዲሞክራሲያው አግባብ መፍትኄ ሊበጅለት ይገባል የሚለው የኢሕአፓ አቋም ያልተመቻቸው ጽንፈኛ ቡድኖችም (ብሔርተኞች) ሰይፋቸውን በድርጅቱ ላይ መዘዙ። የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሆኑት እነዚህ ኃይሎች ይህ ነው የማይባል ሰፊ ጥቃት በኢሕአፓ ላይ ከፈቱ። ዘግናኝ ጭፍጨፋም ፈጸሙበት።

በትግል ወላፍን ተፈትኖ ያደገና የኖረ ትውልድ ያሳለፋቸውን አርባ ሰባት (47) ድፍን የትግል ዓመታት መለስ ብለን ስንቃኝ በሀገራችን ያለማቋረጥ የተፈራረቁት ኋላቀር ፤ አምባገነንና ጎጠኛ አገዛዞች ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሰባስብው በለውጥ ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ በተለይም በኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ጭፍጨፋና ግድያ፤ እስራትና ሰቆቃ ፈፅመዋል። ያ ! ብሩህና አዲስ ተስፋን ለአገሩና ለሕዝቡ ሰንቆ የተነሳ ትውልድ የተመተረበት የጥፋትና የጨለማ ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። ዛሬም ቢሆን የተለወጠ ነገር የለም ስንል አንዱ ማስረጃችን ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች በወያኔ ሰላዮች/ካድሬዎች ታፍነው ደብዛቸው የጠፋው በርካታ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች እሰከዛሬ ድርስ መዳረሻቸው ሳይታወቅ መቅረቱ ነው።
ኢሕአፓ ዘመን ቢቀያየር፤ ገዥዎች ቢፈራረቁ በሕዝቡ ጥቅምና መብት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር፤ በጥቅምና በሥልጣን የማይደለል፤ በጠላት ጊዜያዊ ጥናካሬ ፍፁም የማይሸበርና የማይንበረከክ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ኃያልነትና አቸናፊነት ላይ ጽኑ እምነት ያለው ደርጀት ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ አገራዊ ጥቅም በረጅሙ አማትሮ የሚቃኝ የሕዝብ ልጅ መሆኑን ዛሬም በሚወስዳቸው አቋሞቹ የሕዝብና የአገር አለኝታነቱን በሚገባ አረጋግጧል። ለዚህም ምስክሩ የተመክሮ ተግባሩና በተመክሮው ያካበተው አኩሪ የትግል ታሪኩ ነው።

ስለ ኢሕአፓ በጥቂቱ ይህንን ካልን ዘንዳ በመቀጠል በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ሳያባራ የቀጠለውን የጥፋት ዘመቻ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክራላን። በጎሳና በሃይማኖት ልዩነቶች ምክንያት ዛሬ በመላው አገሪቱ ሊባል በሚቻልበት ሁኔታ ሰላም ጠፍቶ የርስ በርስ ግጭትና መፈናቀል የሕዝብን ህልውናና የአገሪቱን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተፈታተነ ይገኛል። በጎሳ ግጭት የተነሳ በመላ አገሪቱ ከሦስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ከቀየው ተፈናቅሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ተገድለዋል፤ በርካቶች አካለ ጎደሎ ሆነዋል፤ ለፍተው ጥረውና ግረው ያፈሯቸው ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ የቀለሱዋቸው ጎጆች ሳይቀሩ በላያቸው ላይ በእሳት ጋይተዋል። በአሃዝ ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ የሚሆኑ ለነገይቷ ኢትዮጵያ ዋስትና የሚሆኑ ወጣት ተማሪዎች በሰላም እጦት የተነሳ ከትምህርት ገበታቸው ላይ ሳይወዱ በግድ እንዲስተጓጎሉ

ተደርጓል። በርካታ አብያተ ከርስቲያናትና መስጊዶች ሳይቀሩ በእሳት ጋይተዋል። የቱሪስት መስህብ የሆኑ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና እፅዋት በእሳት ቃጠሎ ለአደጋ እንዲጋለጡ ተደርገዋል።
ዛሬ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች ሰላምና መረጋጋት የለም። አማራው ከኦራሞው፤ ኦሮሞው ከጌዲዎው፤ ከምባታው ከሀዲያው፤ ሶማሌው ከኦሮማው፡ ሲዳማው ከወላይታው፤ ትግራዊው ከአማራው፤ ቦረናው ከገሪው፤ … ወዘተ እርስ በርሱ እንዲጋጭና ሁሉም “ክልሌን!” ሁሉም “ጎጤን!” እንዲል እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ወያኔ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በመላው አገሪቱ በዘራውና ኮትኩቶ ባሳደገው፤ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝ ከሚለው ይልቅ የጎሳ ፖለቲካ የተነሳ ሁሉም ክልሎች ከመቸውም ጊዜ በበለጠ የየራሳቸውን የክልል ሚሊሺያ ወይም ልዩ ኃይል አደራጅተውና አስታጥቀው ጊዜና ሰዓትን ጠብቆ ለሚያፈነዳው የጥፋት ፈንጂ ግብዓት መሆናቸውን በተጨባጭ እያየን ነው። ከዚህ አስከፊ የጥፋት ዘመቻ ጀርባ ወያኔ መገኘቱም ደግሞ የሚጠበቅ ነው። ሰሚ ጠፋ እንጂ ከዓመታት በፊት ይህንን እኩይ የወያኔ መሰሪ ሴራና በሀገርና በሕዝብ ላይ ሊከተል የሚችለውን አደጋ፣ ጥፋት መጠቆማችን ምን ያህል ለሃገርና ለሕዝብ አንድነትና ሉዓላዊነት ያለንን ፍቅር የሚገልጽ ለመሆኑ መጽሀፍ ገላጭ አያስፈልገንም። ለውጥ አመጣን ባዮቹ የኦህዴድ ሹመኞቹ የሕዝብን ትግል በባእዳን ትእዛዝ አደናቅፈው ዘረኝነትን/ወያኔነትን ለማስቀጠል ተነስተዋል በማለት መቃወማችን የሚያስወቅስና የሚያስወግዝ ሳይሆን ዘግየቶ ለመረዳት እንደተቻለው እሰየው በርቱ የሚያሰኝ ነው። በቅኝታችንና በአቋማችን ጥራት የምንመጻደቅ ሳንሆን ለቀጣዩ የትግል ምዕራፍ የበለጠ እንድንዘጋጅ የሚያበረታታን ነው።


ሀገሪቱን ለመቀራመት ያሰፈሰፉት ፀረ-አንድነት ኃይላት፣ ኢትዮጵያ አገራችን አሁን ያለችበትን አጣብቂኝ ሁኔታ ወደሚመኙት ዓላማቸው ስኬት ለመለወጥ በመጓጓት ላይ መሆናቸውን በተግባር እየገለፁ ይገኛሉ። ምን ጊዜም ቢሆን ይህንን ስኬት ለማየት ከአሁኑ የተሻለ እድል እንደማያገኙ በሚገባ ተረድተውታል። አጋጣሚው ሁሉ ተመቻችቶላቸዋል። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” ነውና ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ያስገኘላቸውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ዓላማቸውን ለማሳካት በርብርቦሽ ላይ ናቸው። ጽንፍኛ ብሔረተኞች በሁለንተናዊ ረገድ አብረዋል። ተደራጀተዋል። ኅብረተሰባቸውን እነሱ በሚፈልጉት የጥፋት አቅጣጫ እንዲያተኩር አድርገውታል። የኃይል ሚዛኑ ወደእነርሱ ጎራ እንዲያደላላቸው ሌት ተቀን በትጋት ይሠራሉ። አገራችንን ለማዳከምና ለመበተን በሚደረገው ሴራ የባእዳኑ ምክርና ችሎታም አልተለያቸውም። የአንድነት ኃይሉን ጎራ ለማዘናጋት በትጥቅ አስፈች ተውኔት ለማማለል ይጥራሉ። የረሳን መስሏቸው ትላንትና “ወራሪዋ አቢሲኒያ“ እያሉ ሲያዋርዷትና ሲረገሟት የነበረችውን ምድር ዛሬ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” (ለአፋቸው) በማለታቸው የሁሉንም ዜጋ ቀልብ የሳቡ መስሏቸዋል። በዚህ እሳቤ የዜጎችን ቀልብ መሳብ ያስደስታል እንጂ አያስከፋም። ያም ሆኖ ግን ነባቢትን ወደተጨባጭ ድርጊት መለወጥ ያስተማምናል፤ ያቀራርባል ያስተባብራል እያዋሀደ የሀገርን መሠረት ያጠናክራል። የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ለዚህ ሂደት ዐብነት ሆኖ ያገለግላል። ጽንፈኞች ከስሜታዊ አባዜ ወደ ምክንያታዊ ባኅርይ እንዲለወጡ ይጠበቅባቸዋል። የጋራ ሀገርን በጋራ እያዳኑ መቀጠል ለሁሉም ይጠቅማል። ይሁን እንጅ ከልብ ሳይሆን ሕዝብን ለማማለል የሚካሄድ ፖለቲካ ቢከፍቱት ተልባ መሆኑን በተጨባጭ እያየነው ነው።
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ከዛሬ 44 ዓመት በፊት ”ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” በሚል የማማለያ ቋንቋ በመጠቀም ሥልጣን እንደያዙት የደርግ መኮንኖች ሁሉ የዛሬዎቹም መሪ ነን ባዮች በተመሳሳይ ቋንቋ የማዘናጊያ አፍዝ- አደንዝዝ ምትሀት በማርከፍከፍ ላይ ይገኛሉ። ይህ ምትሃት ደግሞ የሀገሩ የኢትዮጵያ ጉዳይ በአጥንቱና በደሙ ገበቶ የሚያንሰፈስፈውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ በቀቢፀ ተስፋ እዲዘናጋ ለማድረግ ጊዚያዊ አቅም አግኝቷል። ላለፈው 28 ዓመታት ከነበረው የጨለማ ጊዜ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል መከሰቱን በመገንዝብና የለውጡን ሁኔታ በአስተውሎ እሳቤ

እየተመለከተው መሆኑን ተረድቶ በትዕግሥት እየተጠባበቀ ያለውን “ኢትዮጵያ ሀገሬ” የሚለውን ዜጋ በማዘናጋት የራሳቸውን ዓላማ ለማራመድ ተመችቷቸዋል። “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” የሚለውን ብሂል የሚያቅ ኅብረተሰብ በማር ቅቤ የቀረበለትን መርዝ የማወቅ ችሎታ አለው። አነሰም በዛ ለዘውጋዊ ፖለቲካ መመቻቸት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ወያኔ መሆኑ ባያጠራጥርም አክራሪ ብሔረተኞች ሁኔታውን በማጦዝ የሀገሪቱን የፖለቲካ መልክዐ-ምድር ወደራሳቸው ፖለቲካ አድማስ ለመለወጥ በጥድፊያ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያዊውን ዜጋ እንደግጦሽ ከብት በጎጥና በክልል ተሸብቦ እንዲኖር ማድረገ የዜግነት መብቱን ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ክብሩንና ልዕልናውንም ጭምር መግፈፍ መሆኑን አክራሪ ብሔርተኞች መገንዘብ ሳይችሉ ቀርተው ሳይሆን ፍላጎታቸውና ጥቅማቸው በዚህ መልክ የሚሟላ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ተወልዶ-ካደገበት፤ ልጅ ወልዶ ከብዶ መላ ህይወቱን ካሳላፈበት አካባቢ ወጥቶ ወደየክልልህ ሂድ እየተባለ የሚፈፀመውን ሀገራዊ ወንጀል ዛሬ በሥልጣን ላይ ያሉት ሹሞች አለማስቆማቸው የወንጀሉ ተባባሪ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል፡፡ የዘረኛ ሥርዓት እንዲዘረጋ ጠንሳሶቹና ቀዳሾቹ የነበሩት የወያኔ ባለሥልጣኖች ባርከው፣ ቀድሰው፣ ጠምቀው፤ አሰልጥነውና መርቀው ስለአሰማሯቸው የእነሱን ፈለግ ቢከተሉ የሚያስገርም አይሆንም። ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅልቅ መሠረትና ምንጩ ከወያኔ ድርጅታዊ ፕሮግራም መንጭቶ የጎሳዊ ሕገ-መንግሥት እንዲሆን የተደረገው የደደቢቱ ሳጥናኤል ሰነድ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። ዛሬ በሀገራችን የሚታየው የፖለቲካ፥ የምጣኔ ሀብትና የማኅበራዊ ኑሮ ምስቅልቅል መሠረቱ በጎሳ ላይ የተመሠረተው ይኸው ወያኔያዊ ሕገ-መንግሥት ለመሆኑ አያከራክርም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ቢሆን ምን፣ ያልመከረበትን፣ ተቀብሎ ያላጸደቀውን፤ የአክራሪ ብሔርተኞችን ሰነድ እንኳንስ የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት አድርጎ ሊቀበል ይቅርና እንደ እድር መተዳደሪያ ወረቀት እንኳ ሥፍራ የሚሰጠው አይደለም፡፡ የዘረኞች ሕገ-መንግሥት የታላቅ ሕዝብና ሀገር ሕገ-መንግሥት ለመሆን ብቃት የለውም። በመሆኑም እስከነግሳንግሱ ሰነዱም ሆነ ሥርዓቱ መቀየርና መፍረስ ይኖርበታል። በምትኩም የሕዝብን ይሁንታ ባገኘ ሕገ-መንግሥትና ፍትሃዊ ርቱዓዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ በተመረጠ ሕዝባዊ መንግሥት መተካት ይገባዋል።

በዜግነት፣ በኢትዮጵያዊነት እንጂ በዘርና በቋንቋ ተከፋፍሎ የሚመሠረት መንግሥታዊ ሥርዓት ለሀገራችን ኢትዮጵያ እንደማይበጅ ዛሬ ሳይሆን ገና ስንፈጠር ጀምሮ ዋጋ የከፈልንበት መለያ አርማችን ነው። አሁን የሚታየውም የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ህያው ምስክር ሆኗል። በመሆኑም ዜጎች በኅብረት ተጠናካረው በቋንቋ እና በዘር ክፍፍል የተመሰረተ ሥርዓትን ለመለወጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ማከናውን አለባቸው። ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ሊያስተናግድ የሚችል አስተዳደርን ለማምጣት በኢትዮጵያዊነት በመደራጀት ማንኛውንም የትግል ስልትና አካሄድ የመጠቀም መብቱን እያስከበረ ኃይሉን ለማጠናክር ጥረት ማድረግ ለይደር የሚተላለፍ ተግባር ሊሆን አይችልም። ፖለቲካ ማለት ሀገርን፣ ለሕዝብን ለማስተዳደር በትክክል ማድረግ የሚቻለውን ማድረግ የሚያስችል ክህሎት ነው እሰከተባለ ድረስ መሆን የሚገባውን ሁሉ እየፈፀሙ ታግሎ ዓላማን የማሳካት ኃላፊነት ገና ለሚመጣው ለተተኪው ትውልድ የሚተላላፍ ሀኬት አይደለም።
ጽንፈኛ ብሔረተኞች “ዛሬ ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን” ብለው ደንድነዋል። የመንግሥት ሥልጣን የጨበጠው አካል ያሻቸውን እንዲፈጽሙ አረንጓዴ መብራት አብርቶላቸዋል። ይሀ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ አክራሪ ዘውገኞችን በአጥቂ ደረጃ ሲያሰልፋቸው በገሀድ አያየን ነው። በአንጻሩ ኢትዮጵያዊነትን ያነገቡ የፖለቲካ ኃይሎች በመከላከል ደረጃ ላይ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል። ለዚህም ነው ዛሬ በአገራችን ፈንቃይ – ተፈናቃይ፤ አባራሪ – ተባራሪ፤ ዘራፊ – ተዘራፊ፤ አሳዳጅ – ተሰዳጅ፤ ገዳይ – ተገዳይ ሁኔታ ጎልቶ ሊታይ የበቃው። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በቋንቋ ላይ የተመሠረተው የዘር/የጎጥ ፖለቲካ ጣጣ ያመጣው ውጤት መሆኑ ተደጋግሞ መሰመር ያለበት ነው። ይህ ደግሞ ለማለት የሚባል ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በደቡብ፥

በሰሜን፥ በምስራቅና በምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው ግጭትና የመበታተን አደጋ ዋናው ምልክት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።

ይህ አስከፊ ሁኔታ ከቀጠለና ቅራኔዎች በደም መፋሰስ እየተባባሱ ከሄዱ፤ ሁሉም ወገኖች ተጎጂ ሆነው ሰላም አጥተው፣ ሀገር አጥተው የጎጠኞች ሰለባ እንደሚሆኑ ግልጥ ነው። የቂም በቀል ጦርነቶች፣ ግጭቶች ለሀገር መደረግ ያለበትን ቅዱስ የመተባበርና የአንድነት ተጋድሎን ያደናቅፋሉ። በዘር ከተከፋፈልን፤ በአንድ ድምጽ ተናግረን፤ ክንዳችንን አስተባብረን ፀረ- ኢትዮጵያ ተንኮልና ሴራን ለመቋቋምና ለማክሽፍ ያቅተናል። ዛሬ በሕዝብ መሀል ያሉትን የርስ በርስ ግጭቶች ለማስቆም መረባረብ ወሳኝ ግዳጅ ሆኖ ይገኛል። ግጭቶቹን እያስፋፉ ያሉትን ጎጠኞችና እነዚሁኑ ጎጠኞች አቅፈውና ደገፈው የሚገኙትን ሹመኞች ወጊዱ ማለትና ሕዝባዊ ተቃውሞን በተደራጀና በተጠናከረ መንገድ የማሰማት ታሪካዊ ሀላፊነት የወደቀው በዛሬው ትውልድ ትከሻ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ትናንት የታገለው ፤ ዛሬም ያልተቋረጠ መስዋዕትንትን በመክፈል የሚታገለው የወያኔን ዘረኛ አገዛዝ አስወግዶ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት እንጂ የተለመደውን፤ ያንኑ ለ28 ዓመት የገማና የገለማ ዘረኛ አፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት አድሶ (ወያኔን በኦህዴድ ተክቶ) ለማስቀጠል አይደለም። ኢሕአፓ ለዚህም ነበር እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርችት ገና ከጠዋቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ የተሸረበውን አገር የማፍረስ ሴራና ከሴራው ጀርባ በሀገራችን ላይ እነማን እየዶለቱ እንደሆነ፤ ባለማቋረጥ የአገር አድን የጥሪ ደውሉን ሲያሰማ የነበረው።

ለዚህም ነው ኢሕአፓ የሀገሪቷን አንድነት ጠብቆ የዜጎቿን ዕኩልነትና መብት አስከብሮ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ማኀበራዊና ፖለቲካዊ ሕመም ለመፈውስ መውጫ መንገዱ የሽግግር ሂደት መጀመር አለበት ሲል ከማንም በፊት በድርጅቱ ልሳን በዴሞክራሲያ አቋሙን ይፋ ያደረግው፤ ለተገባራዊነቱም ለዜጎች ሁሉ የትብብር ጥሪውን ያቀረበው። ለመሠረታዊ ለውጥ እንታገል የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ይረጋገጥ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሸጋጋሪ ሹምም ሆነ ሞግዚት አያስፈልገውም ሲል በአደባባይ ተቃውሞውን ያሰማው። ለዚህም ነው እውነቱን ተናግረን ክብራችንን ጠብቀን ከመሸበት እናድራለን ስንል …. ወያኔ የማይታመን ጎጠኛ ድርጀት ነው ፤ አቋሙን ሸፍኖና ሸፋፍኖ የሚያደናግር ፤ ቆዳውን እንደ እስስት የሚቀያይር፤ ቃሉ ከተግባሩ የማይገናኝ መወገድ ያለበት ጸረ-አንድነትና ጸረ-ሕዝብ ድርጅት ስለሆነ ነው አምርረን እንታገለው ማለታችን። እስከዛሬም የወሰዳቸው እርምጃዎቹ ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ እያጠፋት ሳይወድ በግዱ ደግሞ ስለህላዌዋ፣ ስለአንድነቷ፣ ስለጥንታዊ ታሪክዋ እሚቀባጥርበት ሁኔታ ይታያል። ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገራችንን ህልውናና አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ ከመጣሉም በላይ በግብር ያፈረሰና ሀገሪቷም የምትበታተንበትን ሁኔታ ያመቻቸ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚል ቡድን ካለ ወያኔ/ኢሕአዴግ ነው – ዛሬም በተጨባጭ የሚታየው ይህ ነው ማለታችን ነው። የወያኔ የበላይነት በኦሕዴድ ተቀየረ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም። ላለፈው አይጸጸቱም ለሚመጣው አይበለጡም ነውና ካሳለፍነው ተመክሮ አንዳች ትምህርት በመቅሰም አገራችን ከገባችበት ቀውስ ድና ብቅ የምትልበትን መንገድ/ብልሀት መሻት የሀገር ወዳድ ዜጎቿ ግዴታ ነው። ሀገርን በማዳን ሽፋን ከአዲሱ ሹም (ከወያኔው ኦሕዴድ) ጋር በደፈናው ለማበርና ለመተቃቀፍ ዳግም ለመጎንበስ ለሚፈልጉ ምርጫቸውን ለራሳቸው ትተን፤ ሀገር ወዳድ ክፍሎች በበኩላችን ኅብረታችንን እውን በማድረግ ለዘላቂ መፍትሔ ቅድሚያ በመስጠት ኢትዮጵያን ከጽንፈኞች ለማዳን መረባረብ ይኖርብናል። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ ገዥዎች ሕዝብን ያስመረሩና ያጎመዘዙ የፖለቲካ ቧልቶችን እያደሱና በአዲስ ቃላት እያጀቡ እንደገና ሕዝብን ሊያሞኙና ድጋፍ ሊያገኙ ሲጥሩ፤ ለዚህ ተባባሪና አጃቢ ሳንሆን ዕውነቱን በማስረዳት ማንነታቸውን ማጋለጥ መሰረት ማሳጣት ከእኛ የሚጠበቅ ነው። ወያኔንም ሆነ ተለጣፊዎቹን የማናውቃቸው ስላልሆኑ እስቲ ፈትነን እንያቸው የምንለው አይደለም። ወያኔ

ሲመሠረትም ሆነ ጫካ በነበረበት ወቅት እንዲሁም በባዕዳን ኃይሎች ትብብርና እገዛ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ከወያኔነቱ ሳይዛነፍ በጸረ- ሕዝብነትና በጸረ-ኢትዮጵያዊነት መጽናቱን የደም ዋጋ ክፍለን አረጋግጠናል።
ዛሬም ከሹሞቹ ሥልጣን ገበታ ቀርበን ከዋናው ማእድም ሆነ ከፍርፋሪው ለመቀራመት አንዳዳም። የሕዝባችን መብትና የሥልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት ተረጋግጦ፤ የሕዝብ እኩልነት እውን ሆኖ ኢትዮጵያም ተከብራ፤ ለዜጎቿ አኩሪ መጠለያ ሆና የምትገኝበትን ሁኔታ ለማምጣት ነው ስንታገል የነበረው። ዛሬም ትግላችን እየቀጠለ ያለው ይህንኑ እውን ለማድረግ ነው፡፡ ትናንት ፋሽስቱን አገዛዝ ግንባራችን ሳይታጠፍ ስንታገል ቆይተን ዛሬ ሕዝብና አገር ተዋርደው፤ ኢትዮጵያ አስከፊ አደጋ ተጋርጦባት፤ የወያኔን ጎጠኛ ሕገ-መንግስት አቅፎና ደግፎ ቀጣይና አስፈፃሚ የሆነ ቡድን በሥልጣን ተሰይሞ ባለበት ሁኔታ ትግላችን ተጠናክሮና ጎልብቶ ይቀጥላል አንጂ ከቶም የሚቆም አይሆንም። ሀገራችንን ከነጠቁን ዘረኞችና አስመሳይ (ወያኔዎች) ታግለን ማስመለስ አለብን። ይህ ነው ዋናውና መረሳት የሌለበት የዜግነት ግዴታችን። ሕዝብ በዕኩልነት የሀገሩና የመብቱ ባለቤት ሲሆን፤ የሕዝባችን ሉዓላዊንቱም ሲረጋገጥ ያኔና- ያኔ ብቻ ነው የዜግነት ግዴታችንን ተወጣን ማለት የምንችለው።

አንድነት ኃይል ነው !!!

ኢትዮጵያን ከጽንፈኞች እንታደግ !!!


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE