ሐሳብን በመግለጽ እና በመደራጀት ነጻነት ላይ የሚደረግ ሕገወጥ ገደብ እና የለየለት ጥቃት የአምባገነናዊ አገዛዝ ማቆጥቆጥ የማያሳስት ምልክት ነው።

ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ

ሐሳብን በመግለጽ እና በመደራጀት ነጻነት ላይ የሚደረግ ሕገወጥ ገደብ እና የለየለት ጥቃት የአምባገነናዊ አገዛዝ ማቆጥቆጥ የማያሳስት ምልክት ነው። ይልቁንም ድርጊቱ ሲደጋገም አስተዳደሩ ወይም የአስተዳደሩን ክፍሎች በስውር የመዘወር አቅም ያጎለበቱ ስውር ቡድኖች የዜጎችን መብት ለማክበር ፍላጎት እንደሌላቸው የሚያሳይ ይሆናል።

እስክንድር ነጋ አባል የሆነበት የቴሌቪዥን ጣቢያ (ሰናይ) መቋቋሙን ለማወጅ የተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሁለት ጊዜ ተከልክሏል። ይህ መግለጫ ለኢትዮጵያ መንግሥት ወይም በመንግሥት ውስጥ ላሉ ሹመኞች (ቡድኖች) የስጋት ምንጭ የሆነው ለምንድን ነው? ማፈን፣ ማጥቃት የተፈለገው ማንን ነው? እስክንድርን [ግለሰቡንና የባልደራስ ንቅናቄውን] ወይስ አዲሱን ቴሌቪዥን ጣቢያ ወይስ ሁለቱንም?! መልሱ የትኛውም ቢሆን የክልከላውን ስህተትነትና አደገኛነት አይቀንሰውም።

የሆቴሎቹን አስተዳደሮች የክልከላው ዋና ባለቤቶች አድርጎ በማቅረብ፣ ሐላፊነቱን በእነርሱ ላይ ለመደፍደፍ መሞከር ፖለቲካዊ ቂልነት ነው። ቂልነት ለራስ ነው። ሆቴሎቹ የገቡትን ውል በማፍረስ ጋዜጣዊ መግለጫዎቹ እንዲሰረዙ አድረገዋል ቢባል እንኳን፣ እርምጃው በመነሻውም ሆነ በውጤቱ ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው መሆኑን የሚቀንሰው አይሆንም። ሆቴሎች ሥራቸው አዳራሽ ማከራየት እንጂ አዳራሹ ውስጥ የሚነገረውን መቆጣጠር፣ ሳንሱር ማድረግ አይደለም። እነእስክንድር በጋዜጣዊ መግለጫው ሕገ ወጥ ተግባር ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚል በማስረጃ ላይ የተመሠረት ግምት ስለመኖሩም ሆቴሎቹም ሆኑ ፖሊስ የገለጹት ነገር የለም። ስለዚህም፣ ፖሊስም ሆነ መንግሥት የጉዳዩን መዘዝ በፌስቡክ ማስተባበያ እንመልሰዋለን ብለው ራሳቸውን ሊዋሹ አይገባም።

ገና ከጅምሩ፣ ሆቴሎቹ ውላቸውን አፍርሰው፣ ገቢያቸውን ትተው ጋዜጣዊ መግለጫዎቹን የሚሰርዙበት ምክንያት በገበያ ሕግ የሚተነተን ሳይሆን፣ እያገነገነ ካለው ፖለቲካዊ አየር የሚቀዳ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። የመንግሥት የጸጥና የደኅንነት መሥሪያ ቤቶችን (ፖሊስ፣ መከላከያ እና የስለላ ክፍሉ) ከውርስ በሽታቸው መፈወስ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ እረዳለሁ። የለውጥ ሙከራው በተበላሸ መሠረት ላይ እየተካሄደ እንደሆነ እገነዘባለሁ። ሆኖም፣ ተቋማቱ እንዲህ አይነቱን ጋጠ ወጥ ተግባር በአደባባይ ሲፈጽሙ ወይም (እንደሚባለው) የአንድ ቡድን የፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ ሲሆኑ ዝም ብሎ መመልከት ከስሕተታቸው እንዲማሩ የሚያደርግ አይሆንም።

የሆቴሎቹ አስተዳደሮች በይፋዊና ይፋዊ ባልሆኑ የመንግሥት ተጽዕኖዎች ሥራቸውን እንዳያከናውኑ የሚደረግበት አሠራር መመርመርና መታረም አለበት። የአዲሳባም ይሁን የፌዴራል ፖሊስ (ወይም መንግሥት) ጉዳዩን መርምሮ እያረመ፣ ይህንንም ለሕዝብ እየገለጸ ካልተጓዘ፣ አያያዙ ወዴት እንደሚያመራ እናውቀዋለን። ሆቴሎቹ ራሳቸውም ቢሆኑ፣ ከመንግሥት አካላት የሚደርስባቸውን ጣልቃ ገብነት በማኅበራቸው በኩል መታገል ይኖርባቸው ይሆን?

በመጨረሻ፣ እንዲህ አይነቱን ተግባር ጠ/ሚሩ ወይም ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያውቁታል አያውቁትም የሚል ክርክር ጠቃሚ አይደለም። እነርሱ ዝርዝሩን አስቀደመው አወቁም አላወቁም፣ በመስተዳድራቸው ለሚፈጸሙ ስሕተቶች ተወቃሽ/ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። አዲሳባ ውስጥ የሚደረግ ሲሆን ደግሞ፣ ሐላፊነቱን ለክልሎች ለመስጠት እንኳን አይመችም።
ሲሆን ሁሉንም መብቶች ማክበር ማስከበር ነው፤ ሲያቅት ደግሞ፣ ስሕተቶች ከተሰሩ በኋላ በተቻለ ፍጥነት መመርመርና ማረም ነው።

መሠረታዊ መብቶችን ማክበር፣ አለማክበር፤ ይኸው ነው ጥያቄው!
መሠረታዊ መብቶችን ማስከበር፣ አለማስከበር፤ ይኸው ነው ጥያቄው!

========================
ቅድመ ሁኔታዎች እና ደንቦች ተፈጻሚ ይሆናሉ!
ቅድመ ሁኔታው፤ ሐሳብና መረጃ ለመለዋወጥ መፍቀድ
ደንቡ፤ መድረኩ ስድብና ከርዕሰ ጉዳይ ወጥቶ መዘባረቅን አያስተናግድም።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE