97 የአማራ ተወላጅ የፖለቲካ እስረኞች የት እንደገቡ አልታወቀም

97 የአማራ ተወላጅ የፖለቲካ እስረኞች የት እንደገቡ አልታወቀም (Getachew Shiferaw)

~ባለፉት ሳምንታት የፖለቲካ እስረኞች ተቃውሞ እያሰሙ ይገኛሉ። እስረኞቹ መንግስት ክስ ማንሳቱን፣ ፍርድ ቤቱም በተነሳ ክስ ላይ የተከሳሽ ጉዳይን የማየት ስልጣን እንደሌለው በመግለፅ ወደ ፍርድ ቤት አንሄድም ብለዋል።

~ሆኖም ፍርድ ቤቱ አልቀረቡም ያላቸውን ተከሳሾች በሌሉበት እስከ አንድ አመት እየቀጣ፣ ቅጣቱን በደብዳቤ ይልክላቸዋል። ተከሳሾች ውሳኔውን አንቀበልም ይላሉ።

~የቂሊንጦ እስር ቤት ፍርድ ቤት ባልተገኙበት የተፈረደባቸውን የፖለቲካ እስረኞች ወደ ቃሊቲ እንዲዛወሩ ሲጠይቅ ተከሳሾቹ ተቃውመዋል። አንዱ የተቃውሞ ምክንያት ከአንድ ወር በፊት ገበየሁ ፈንታሁን የተባለ የባህርዳር ልጅ ወደ ቃሊቲ በተዛወረ በሁለተኛ ቀኑ ለህልፈት በመዳረጉ ነው። ይህ ወጣት ከእነ ሙሉ ጤናው ወደ ቃሊቲ ተዛውሮ ለህልፈት መዳረጉ ሌሎች ተከሳሾች ላይም ስጋት ፈጥሯል።

~ሚያዝያ 30/2010 ዓም በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል ብይኑን አንቀበልም በማለታቸው በተነሳ አለመግባባት ችሎት በመቋረጡ ቂሊንጦ እስር ቤት ያለ ስልጣኑ እስረኞችን ቀጥቷል። ጨለማ ቤት አስገብቷል። ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። ወደ ዝዋይና ወዳልታወቀ እስር ቤት ተዛውረዋል።

~የቂሊንጦ እስር ቤት የፖለቲካ እስረኞችን ወደ ቃሊቲና ወደ ዝዋይ ለመጫን ሲሞክር ከእስረኞች ተቃውሞ ገጥሞታል። ተከሳሾች በሚደርስባቸው በደል የርሃብ አድማ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት እስር ቤቱ ግንቦት 2/2010 ዓም በጠዋት የሚጀመረውን የቤተሰብ ጥየቃ ከልክሎ በየማማው መሳርያዎችን በመጥመድና በርካታ የፖሊስ ሀይል በማዘጋጀት ሲያስፈራራ እንደነበር ታውቋል።

~የቂሊንጦ እስር ቤት 150 የፖለቲካ እስረኞችን ወደ ሌላ እስር ቤት ለማዛወር ከየዞን ግቢያቸው አስወጥቶ እንደነበር ታውቋል። ሆኖም ሁለቱን ነጣጥሎ ለማሰር ሲባል 97 የአማራ ተወላጆችን ወዳልታወቀ ቦታ ሲወስድ፣ 53 የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ቂሊንጦ ተመልሰዋል ተብሏል።

~የቂሊንጦ እስር ቤት ግልፅ ባልሆነ ምክንያት በ”ሽብር” የተከሰሱትን እስረኞች በአንድ ግቢ በመሰብሰብ (ዞን 1) አንድ ግቢ ውስጥ እንዲሆኑ አድርጎ የነበር ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአማራና ኦሮሞ ተወላጆችን እየነጣጠለ ነው ተብሏል። ከቂሊንጦ የተወሰዱት 97 የአማራ ተወላጅ የፖለቲካ እስረኞች የት እንደገቡ አልታወቀም ተብሏል።