በ1ሺህ 34 ህገ-ወጥ አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በ1ሺህ 34 ህገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለፀ

በ1ሺህ 34 ህገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ገለፀ።

ቋሚ ኮሚቴው በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ የመስክ ምልክታ አድርጓል።

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው የተገኙ ግኝቶችንም የኢፌዲሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አቅርቧል።

በዚህም የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አዋጅ በተለያዩ ምክንያቶች ለአራት አመታት ወደ ስራ መግባት አለመቻሉን ፣ የሀገር ውስጥ ስራና ሰራተኛ በማገናኘት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ኤጀንሲዎች የህገ-ወጥነት መስፋፋት ፣ የፌደራል የአሰሪና ሰራተኞች አማካሪ ቦርድ ተጠናክሮ ወደ ስራ አለመግባት ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው ካገኛቸው ግንቶች ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጿል።

Image may contain: 2 people, people sitting

ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ክትትል ያለ ፈቃድ ሲሰሩ ባገኛቸው 1ሺህ 34 ህገ-ወጥ ኤጀንሲች ላይ እርምጃ መውሰዱም ተነግሯል።

ኤጀንሲዎች የውሸት ክፍት የስራ ቦታ በማውጣት ከስራ ፈላጊዎች በተለይም ከዲግሪ ምሩቃን ከብር 400 እስከ 8ሺህ እንደሚቀበሉ ተደርሶበት ፈቃድ የመሰረዝ ስራ መሰራቱም ተገልጿል።

ከስራ ፈላጊዎች ብር የተቀበሉት ኤጀንሲዎች ከፈቃድ ስረዛው ባሻገር ወደ ህግ ቀርበው እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያብራራው።

ሰራተኞቹ በሀገር ውስጥ አሰሪ ኤጀንሲዎች የሚፈጸምባቸውን ዘመናዊ ባርነት ለመሸሽ ለህገ-ወጥ ስደት እየተዳረጉ መሆኑንም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል።

ለሰራተኞቹ የሚከፈለው ደመወዝ አነስተኛ የሚሆነው አሰሪ ኤጀንሲዎች ቫትን ጨምሮ የተለያዩ ክፍያዎችን ከሰራተኞቹ ደመወዝ ቀናንሰን ለመንግስት ስለምንከፍል ነው ሲሉ መናገራቸውም ተጠቁሟል።

በሰራተኞች ላይ ዘመናዊ ባርነት አንፈጽምም፤ ጉዳዩ በማን እተፈጸመ እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው ክትትል ቢያደረግ እውነታው ላይ መድረስ እንደሚችልም ተጠቁሟል።

ሰራተኞች የመደራጀት መብት ተነፍጎናል ሲሉ በተለያየ ጊዜ ቅሬታ እንደሚያነሱ የሴቶች ፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ ተናግረዋል።

ሁሉም አሰሪ ኤጀንሲ መደራጀት መብት መሆኑን አውቀው በመንቀሳቀስ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ከመስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተከፍቷል በሚል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ከተነገረ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ የአለመጀመሩና ለስራ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱ ሰራተኞች ቢያንስ የ8ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ መሆን ይገባል በሚል መገደቡ ትክክል እንዳልሆነ ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ምልከታው ማረጋገጡን ጠቅሷል።

ከሰራተኛ ተቀባይ ሀገራት ጋር የሚደረገው ውይይት በታሰበው መልኩ መቀጠል አለመቻሉ ለስምሪቱ መዘግየት መንስኤ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናግረዋል።

ከስምንተኛ ክፍል ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም ሰራተኞቹ ማንበብና መጻፍ ችለው መብትና ግዴታዎቻቸውን አውቀው እንዲንቀሳቀሱ ታስቦ የተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አክለዋል።

የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አዋጅ በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ የሰራተኛና ማህበረዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መስራት እንደሚገባው ወይዘሮ አበባ ማሳሰባቸውን የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።