አዴፓ የፓርቲዉን ስምና የክልሉን ርዕሠ-መስተዳድር ከመቀየር ባለፍ ለአማራ የተከረዉ ነገር የለም – ደብረብርሐን

የደብረብርሐን እና የአካባቢዉ ነዋሪ የአማራ ሕዝብ መብት እንዲከበር በአደባባይ ሰልፍ ጠየቀ።በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ርዕሠ ከተማ የሆነችዉ የደብረ ብርሐን እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት የአማራ መስተዳድር ገዢ ፓርቲ አዴፓ የፓርቲዉን ስምና የክልሉን ርዕሠ-መስተዳድር ከመቀየር ባለፍ ለአማራ የተከረዉ ነገር የለም።

የሸዋ አማራዎች የተባለዉ ስብስብ በጠራዉ የአደባባይ ሠልፍ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ መገኘቱን ተሳታፊዎች አስታዉቀዋል።የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን በስልክ ያነጋገረዉ ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ፣ የሸዋ አማራ ወጣቶች ማሕበር ሰብሳቢ ተክለፃዲቅ ግርማ ሰልፈኛዉ ካነሳቸዉ ጥያቄዎች ገሚሱን ይዘረዝራል።ሰልፈኞቹ የደራ፣የወልቃይትና የራያ አስተዳደራዊና የማንነት ጥያቄዎች መልስ እንዳገኙ ጠይቀዋልም።

ሰልፈኞቹ አጣዬ፣ምንጃርና ሸንኮራ በተነሱ ግጭቶች የተገደሉ አማራዎችን ለማሰብም ሻማ አብረተዉ ነበር።የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና የፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢበል ደግሞ ሠልፈኛዉ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አማራን ይበድላል ማለታቸዉን ጠቅሰዋል።አቶ ካሳሁን አክለዉ እንዳሉት ሠልፉ ሠላማዊ ነበር።በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በአማራ ላይ ይደርሳል የሚሉት በደል እንዲቆም በመጠየቅ ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ የአደባባይ ሰልፍ ሲያደርጉ ነበር።