በደቡብ ክልል የሰዉ ነብስ በማጥፋት፣ ሐብት ንብረት በመዝረፍና በማፈናቀል የሚጠረጠሩ ታጣቂዎች ለፍርድ ባለመቅረባቸዉ ሌላ ጥፋት ላለመደገሙ ዋስትና የለም።

በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ በተደረጉ ግጭቶች ከቤት ንብረታቸዉ ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች የተወሰኑት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው እየተመለሱ ነዉ።የመንግሥት ባለሥልጣናትና ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ተፈናቃዮቹ ወደቀድሞ መኖሪያቸዉ የተመለሱት መንግስትና የርዳታ ድርጅቶች ባደረጉላቸዉ ድጋፍ ነዉ።

ይሁንና ሰሞኑን ዋቹና ጭርቁ ወደተባሉ የጌዲኦና የምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ መንደሮች የተመለሱ ነዋሪዎችን ያነጋገረዉ የሐዋሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ እንደዘገበዉ ተመላሾቹ አሁንም ከስጋት አልተላቀቁም።ተመላሾቹ እንደሚሉት ከዚሕ ቀደም ወገኖቻቸዉን ገድለዉ እነሱን ዘርፈዉ ከየመኖሪያቸዉ ያሰደዷቸዉ ታጣቂዎች አሁንም እንደልባቸዉ እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ዳግም ጥቃት ሊያደርሱባቸዉ ይችላሉ።

ተመላሾቹ እንደሚያምኑት የሰዉ ነብስ በማጥፋት፣ ሐብት ንብረት በመዝረፍና በማፈናቀል የሚጠረጠሩ ታጣቂዎች ለፍርድ ባለመቅረባቸዉ ሌላ ጥፋት ላለመደገሙ ዋስትና የለም።ደቡብ ኢትዮጵያ ጌድኦ፣አማሮ፣ቡርጂና ባስኬቶን ጨምሮ በተደጋጋሚ በተደረጉ ግጭቶች በትንሹ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏል።