የአንዳንድ ክልል ሕገ-መንግሥቶች ለመፈናቀሉ ሕጋዊ ከለላ እንደሚሰጡና መፈናቀሉም ሕጋዊ መሠረት እንዳለው አብንና ኢዜማ ተናገሩ

የአንዳንድ ክልል ሕገ-መንግሥቶች ለመፈናቀሉ ሕጋዊ ከለላ እንደሚሰጡና መፈናቀሉም ሕጋዊ መሠረት እንዳለው አብንና ኢዜማ ተናገሩ

አብመድ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምክትል ሊቀ መንበር ዶክተር ጫኔ ከበደን አነጋግሯል፡፡ የፓርቲዎቹ መሪዎች የወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮችን መንስኤና መፍትሔ አስመልክቶ ሐሳቦችን ሰጥተዋል፡፡

እንደ ፓርቲዎቹ ማብራሪያ እየታየ ያለው የመፈናቀል ችግር የተጀመረው ለውጥ ቤተ መንግሥት ላይ ብቻ የተወሰነ እና ወደታች ወርዶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ ደረጃ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ለውጥ አለ›› ተብሎ በሚነገርበት ወቅትም ብዙ ሺህ ወገኖች እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ አንስተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ሕግ እና ሥርዓት በማስከበር ላይ ለዘብተኛ መሆኑን ቀዳሚ ምክንያት አድርገው አስቀምጠውታል፡፡ ‹‹ለውጥ አንዳንዴ መራራ ይሆናል፤ መራራ ክኒን መዋጥ ሊያስፈልግም ይችላል፡፡ ከሕግ እና ሥርዓት ውጭ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፣ ዜጎችን የሚያፈናቅሉ እና የሚያጠቁ የታጠቁ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አለመቻሉ የለዘብተኛነት ማሳያና ቀዳሚ ምክንያት አድርገን ልንወስደው እንችላለን›› ነው ያሉት፡፡

ፓርቲዎቹ ሁለተኛ የመፈናቀል ምክንያት አድርገው ያስቀመጡት ደግሞ ‹ለውጥ› የሚባለው ነገር ከታች አለመድረሱን ነው፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ አማራዎች በሚደርስባቸው ጥቃት እና መፈናቀል ዝቅተኛ የመንግሥት መዋቅር ላይ ያሉ የመንግሥት አመራሮች እና ካድሬዎች ተሳታፊ እንደሆኑ እየተገለጸ መሆኑን በመጥቀስ ‹ለውጡ መሬት አልነካም› ብለዋል፡፡ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ አንድ የመምህራን ኮሌጅ ውስጥ ቀስት እየተመረተ ለጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት የሚያከፋፍሉና አማራዎች እንዲጠቁ የሚያደርጉ አመራሮች እንዳሉ በይፋ ተገልጿል፡፡ ይህ የሚያሳየው እየተባለ ያለው ለውጥ ምኒሊክ ቤተ-መንግሥት ላይ ብቻ የተወሰነና ወደታች ወርዶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ ደረጃ አለመድረሱን ያመልክታል ተብሏል፡፡ በዚህ የተነሳ መፈናቀሉና እየደረሰ ያለው ጉዳት ከባድ እንደሆነና ሀገሪቱንም መንታ መንገድ ላይ እንደጣላት ገልጸዋል፤ መፈናቀሉ ኢትዮጵያን ከዓለም ቀዳሚ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የዘር (የማንነት) ትርክት በስፋት እየተነገረ እና ብዙ ወጣቶችን እያሳተፈ የመጣበት ሂደት እንደነበርና እነዚህ አካላት ‹‹የለውጥ ኃይል ናቸው›› ተብለው መወሰዳቸውና የዘር ፖለቲካ በሕግ ማዕቀፍ መደገፉ ችግሩን እንዳባባሰው አብራርተዋል፡፡ የችግሩ መነሻም የዘር ትርክት አራማጆችን የለውጥ ኃይል አድርጎ መውሰዱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ለውጡ ጥሩ ሆኖ እያለ የሕግ የበላይነት ቅድሚያ መከበር ያለበት መሆኑን መረዳት መቻል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አንድ ሕዝብ ‹‹መንግሥት አለኝ›› ካለ ሕይወቱ፣ ቤቱ፣ ንብረቱና ቤተሰቡም በመንግሥት መጠበቅ እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት፡፡ እንደ ፓርቲዎቹ ማብራሪያ ሕዝብ ስልጣኑን ለመንግሥት ሰጥቷል፤ መንግሥት ደግሞ የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ አለበት፡፡

የነበረው የደኅንነት መሥሪያ ቤት በሴራ ፖለቲካ የተተበተበ የነበረ መሆኑንና ለውጡ ሲመጣ እና መለወጥ ሲጀምር በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ ባጠቃላይ ወደ ሴራ ፖለቲካ መግባታቸው አሁን ላለው ችግር አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በደኅንነት ተቋሙ ውስጥ የነበሩት የዘር ፖለቲካ አራማጆች የጥላቻ ፖለቲካ ሕዝቡ እንዲገባ ማበረታታት መጀመራቸውንና የቆየውን መዋቅር ለጥላቻ፣ ለጸብ እና ለግጭት እየተጠቀሙት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ መንግሥት ይህንን መሥሪያ ቤት አፍርሶ በአዲስ ማዋቀር እንደነበረበትም አስታውቀዋል፡፡

የፖሊስ ሠራዊት ጉዳዩን ለመከታተል በሚያስችል አደረጃጀት ወዲያውኑ መስተካከል እንደነበረበትም አመልክተዋል፡፡ የፖሊስ ሠራዊት ባለበት እንዲቀጥል መደረጉ አብዛኛው የፖሊስ አካል ሕግን ከማስከበር ይልቅ መሀል ሰፋሪ ሆኖ እንዲቆም እንዳደረገውም አስረድተዋል፡፡ የሚፈጠሩ ግጭቶችንም ‹‹አይመለከተኝም›› በሚል ስሜት እየተመለከተ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ይህ ትልቅ አደጋ ነው፤ ሕግን ለማስከበርም ትልቅ ክፍተት ነው›› ብለዋል፡፡

ግጭቶችንና መፈናቀሎችን የሚቀሰቅሱ ጊዜያዊም መሠረታዊም ምክንያቶች እንደሚኖሩ ያስገነዘቡት የፓርቲዎቹ መሪዎች ‹‹በጊዜያዊነት በሕዝቦች መካከል ግጭቶችን ቀስቅሰው ለማፈናቀል ምክንያት የሚሆነው ከተፈጥሮ ሀብት ጋር የተያያዘ ፉክክርና ያንን ሀብት ለመቆጣጠር እና ለማግኘት የሚደረግ እንቀርስቃሴ ናቸው›› ብለዋል፡፡ መሠረታዊ ምክንያቶቹ ግን ከኢህአዴግ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ መልክ፣ መንግሥታዊ መዋቅርና የሕዝቦች ትስስር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀየር መደረጉ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ የፌደራል ሥርዓቱ ሲዋቀር ቋንቋንና ማንነትን መሠረት አድርጎ መሆኑና ክልሎችም ሲደራጁ እንዲሁ ዘርን መሠረት አድርጎ መሆኑ ችግር መፍጠሩን አስገንዝበዋል፡፡

በብዙዎቹ አካባቢዎች ላይ አንድ ክልል ላይ የሚኖሩ የተወሰኑ ብሔር ብሔረሰቦች የክልሉ ባለቤት መደረጋቸው ትልቅ ስህተት መሆኑን ያመለከቱት ፓርቲዎቹ በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደ አማራ ያሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሕዝቦች የክልሉ ባለቤት አለመሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የክልሉ ባለቤት ብሎ የሚያስቀምጣቸው ጉሙዝ፣ በርታ፣ ሽናሻ፣ ማኦ እና ኮሞ ብሔረሰቦችን ነው፡፡ በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች እንደ ሕጋዊ የክልሉ ነዋሪነት አይቆጠሩም›› ነው ያሉት፡፡
‹‹ዴሞክራሲ ብለህ ብሔር የለም፤ ብሔር አለ ብለህ ዴሞክራሲን መገንባት አትችልም፤ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በራሱ ልዩነትን እየፈጠረ የሚሄድ እንጅ ዴሞክራሲን የሚያሳድግ አካሄድ አይደለም፡፡ በትንሹ የኔ ዘር ከተከበረ፣ የኔ የቋንቋ ወሰን ከተከበረ፣ የኔ ወረዳም ይሁን ዞን ደንበሮች እና ወሰኖች ከተከበሩልኝ ከዚያ ተነስቸ ከሌላው ጋር በራሴ ስምምነት አገር እየገነባው እሄዳለው የሚል ነው፡፡ ልዩነቶችን እየፈጠረ የመጣውም ይህ ነው፤ ከዚህ ተነስቶ አድጎ መጨረሻ ላይ የደረሰው ‹ይህ መሬት የኔ ነው፤ ከዚህ ወንዝ ማዶ እንዳትሻገር፤ ይህ ሀብት የኔ ነው› ማለት ነው የተጀመረው›› ሲሉም ግጭቶች የሥርዓቱ ሂደት ውጤቶች መሆናቸውን አንስተው ሞግተዋል፡፡

በታሪክ አጋጣሚ ብሔር ብሔረሰቦች በኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሀብት ለማፍራትና ኑሮ ለመመሥረት በብዙ አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ብሔረሰቦች ‹‹ከዚህ መለስ ያንተ አይደለም፤ መጤ ነህ›› የሚል ስም እየተሰጠው እንዲፈናቀል ተደርጓል፡፡ አይደለም ኢትዮጵያዊ ወገኑን ከሌላም ሀገር ቦታ የመጣን ‹መጤ› ማለት ተገቢ እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡

ማንኛውም ነገር ሲነሳ ‹‹ሕገ-ወጥ ናቸው፤ የባለቤትነት መብትም የላቸውም፤ ሰፋሪ ናቸው፤ ስለዚህ ለቅቀው ይውጡ›› የሚል ሁኔታ እንዲፈጠር መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ የተተከለው የፌደራል ሥርዓት ቋንቋን ብቻ መሠርት አድርጎ አግላይ በሆነ መንገድ መተከሉ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰቱ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት እንዲከሰት ያደረገ በመሆኑ ሊጠና እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

አማራ ክልል ላይ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የመፈናቀል ችግር አለመኖሩን ያመለከቱት ፓርቲዎቹ ‹‹ከአማራ ክልል በፖለቲካው ተነሳስተው ከሄዱት ውጭ በማንነት ምክንያት ሰው አልተፈናቀለም፡፡ የክልሉ ሕገ-መንግሥት ‹የክልሉ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት እና የክልሉ ባለቤቶች የክልሉ ነዋሪዎች ናቸው› ይላል እንጅ አንድን ብሔር ብቻ ለይቶ ባለቤት አያደርግም›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ዜጎች በየትኛውም ሁኔታ ተንቀሳቅሰው በሚመርጡት አካባቢ መኖሪያቸውን የማድረግና የመሥራት ዕድል እንደሚሰጥ ያመለከቱት የፓርቲዎቹ መሪዎች የክልሎች ሕገ-መንግሥቶች በተለይም የኦሮምያ እና የቤኔሻንጉል ጉሙዝ ችግር እንዳባቸው በመግለጽ መስተካከል ያለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡